ትልቅና መርዛማ የሸረሪት ዝርያ አውስትራሊያ ውስጥ ተገኘ
ሸረሪቱ 1.97 ኢንች ከሚረዝመውና ከተለመደው የስድኒው ፈነልዌብ ሸረሪት ጋር ሲነጻጸር እስከ 3.54 ኢንቺ ማደግ የሚችል ነው
ተመራማሪው ክርስቴንሰን ሸረሪቱ "በጣም ግዙፍ፣ የመርዝ አመንጭ እጢው ከፍያለና ጥርሱም ረዘም ያለ ነው" ብለዋል
ትልቅና በጣም መርዛማ ከሆኑት የዓለም የሸረሪት ዝርያዎች ውስጥ እጅግ አደገኛ የሆነው በአውስትራሊያ ሳይንቲስቶች ተገኝቷል።
ሸረሪቱ ከተለመደው እና 1.97 ኢንች ከሚረዝመው የስድኒው ፈነልዌብ ሸረሪት ጋር ሲነጻጸር እስከ 3.54 ኢንቺ የሚያድግ ሲሆን 'ቢግ ቦይ' የሚል ተሰጥቶታል።
"ይህ ሸረሪት በጣም ግዙፍ፣ የመርዝ አመንጭ እጢው ከፍያለና ጥርሱም ረዘም ያለ ነው" ሲሉ የሸረሪት ተመራማሪው ካኔ ክርስቴንሰን ተናግረዋል። የስድኒ ፈነልዌብ በፈጣን እርምጃቸው እና በመርዛቸው የሚታወቁ ሲሆን እንደመታደል ሆኖ አዲሶቹ ዝርያዎች በመንደፍ ለሚያደርሱት ጉዳት ተመሳሳይ ጸረ- መርዝ መድሃኒት ውጤታማ ነው።
ክርስቴንሰን 'ቢግ ቦይን' ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኙት በሰሜን ስዲኒ ኒውካስትል አቅራቢያ በ2000 መጀመሪያ ሲሆን እሳቸውን ለማስታወስ አትራክ ክርስቴንሰኒ የሚል ሳይንሳዊ ሰያሜ ተረጥቶታል።
"አንዳንዴ ገራዥ ውስጥ፣ መኝታ ቤት ውስጥ ወይም ቤት ውስጥ የትኛውም ቦታ ምሽት ላይ ሲንቀሳቀሱ ልታገኟቸው ትችላላችሁ" ሲሉ የቀድሞው የአውስትራሊያ ፓርክ የሸረሪት ዳይሬክተር ክሪስተንስን ተናግረዋል።
"እንድትነኳቸው በፍጽም አልመክርም። በእርግጠኝነት ይነድፏችኋል።"
ከአውስትራሊያ ሙዚየም፣ፍሊንደርስ ዩኒቨርስቲና ከጀርመኑ ሊበንዚ ኢንስቲትዩት የተውጣጡ ሳይንቲስቶች 'ቢግ ቦይ'ን የተለየ ዝርያ አድርገው ባለፈው ሰኞ መድበውታል።እነዚህ የሸረሪት ዝርያዎች ከስድኒ ከ160 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ ሲሆን ወንዱ ዘርያ ተቃራኒ ጾታ ለማግኘት በሚወጣበት ከህዳር እስከ ሚያዝያ ባለው ጊዜ ውስጥ በጣም አደገኛ ናቸዉ ተብሏል።
13 ሰዎች በእነዚህ ሸረሪቶች ተነድፈው የሞቱ ሲሆን ጸረ-መርዙ ከተመረተ ከ1981 ወዲህ ግን ሞት አልተመዘገበም።