የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ በማሰብ የ17 ሚሊየን ብር የመንግስት ሃብት ያለአግባብ እንዲባክን ማድረጋቸውን ፍርድ ቤቱ አስታውቋል
በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የደብረብርሃን ከተማ አመራሮች ፍርድ ቤት ቀረቡ
በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት የደብረ ብርሃን ከተማ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችና ሙያተኞች ዛሬ በሰሜን ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበው የ15 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል።
የስራ ኃላፊዎቹ ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም እና ከከተማ መሬት ጋር በተያያዘ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ነበር ከትናንት በስቲያ መጋቢት 9 ቀን 2012 ዓ.ም በቁጥጥር ስር የዋሉት።
ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ በካሬ 36 ሺህ ብር የሚያወጣ የከተማ ቦታ ስልጣናቸውን ያለአግባብ በመጠቀም ከ15 ሺህ በታች በማስተላለፍ መጠርጠራቸውን በንባብ አሰምቷል።
የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ በማሰብ የ17 ሚሊየን ብር የመንግስት ሃብት ያለአግባብ እንዲባክን አድርገዋል በሚል የተጠረጠሩ ናቸው ።
ችሎት የቀረቡት ተጠርጣሪዎች በጠበቃቸው በኩል የዋስትና መብት ይጠበቅልን የሚል ክርክር አቅርበው ዓቃቤ ህግ ወንጀሉ ከፍተኛ በመሆኑ ዋስትና እንዳይሰጣቸው ተቃውሞ አቅርቧል።
ከፍተኛው ፍርድ ቤቱ የተፈጸመው ወንጀል ከ10 ዓመት በላይ ሊያስቀጣ የሚችል ከባድ ወንጀል በመሆኑ የቀረበውን የዋስትና መብት ውድቅ በማድረግ የ15 ቀነ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ዓቃቤ ህግም አስፈላጊውን ማስረጃ በማሟላት በተቀጠረው ቀን ክስ እንዲመሰርት ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ አስተላልፏል።
ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጠርጥረው ዛሬ ከቀረቡት መካከል የደብረ ብርሃን ከተማ ምክትል ከንቲባው አቶ ደስታ አንዳርጌ ፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ጽህፈት ቤት ሀላፊው አቶ ተሰማ አማረና የገቢዎች ጽህፈት ቤት ሀላፊው አቶ መክቴ ሰብስቤ ይገኙበታል ።
በተጨማሪም የከተማው የመሬት ልማት ማኔጅመንት ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ደምሴ ተፈረደኝና የአገልግሎት ጽህፈት ቤት ባለሙያው አቶ ሀይሉ ሽፈራውም ተጠርጣሪዎች ሆነው ቀርበዋል፡፡