ከደብረ ብርሀን- ደሴ የትራንስፖርት አገልግሎት ከተቋረጠ አንድ ወር ሞላው
መንገዱ በመዘጋቱ ምክንያት ህክምና የሚፈልጉ ሰዎች ለከፋ አደጋ መዳረጋቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል
መንገዱን የዘጋው የሰሜን ሸዋ ኮማንድ ፖስት ይህ መንገድ መቼ እንደሚከፈት ከመናገር ተቆጥቧል
ከደብረ ብርሀን-ደሴ የትራንስፖርት አገልግሎት ከተቋረጠ ዛሬ አንድ ወር ሆኖታል።
በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች መካከል ባለፈው አመት ሚያዝያ የተጀመረው ጦርነት እስካሁን መቋጫ አላገኘም።
የሰሜን ሸዋ ዞን ኮማንድ ፖስት በ"ጽንፈኞች" ላይ እርምጃ ለመውሰድ በሚል ከካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ከደብረ ብርሀን- ደሴ እና ከደሴ- ደብረ ብርሀን የየብስ ትራንስፖርት መቋረጡን አስታውቆ ነበር።
ይህን ተከትሎም በዚሁ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ለከፋ እንግልት መዳረጋቸውን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአጣዬ ከተማ አስተያየት ሰጪ ወደ ደብረ ብርሀን እና ደሴ የሚያስኬደው ዋናው የአስፓልት መንገድ በመዘጋቱ ምክንያት ሸቀጦች እየገቡ አይደለም ብለዋል።
ወደ አዲስ አበባ የሚያስኬደው መንገድ በመዘጋቱ ምክንያት በመሀል ሜዳ በኩል መጓዝ የግድ በመሆኑ ምክንያት ከዚህ በፊት ከአጣዬ-ደብረ ብርሀን የነበረው የትራንስፖርት ዋጋ ከ200 ብር አሁን ወደ 500 ብር ከፍ ብሏልም ብለውናል።
ሌላኛው ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ለእረፍት በሚል ከሚማርበት አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ቤተሰብ ለመጠየቅ ወደ ደሴ ማምራቱን ገልጾ መንገዱ በመዘጋቱ ምክንያት የግድ ቤተሰቡን አስቸግሮ በአውሮፕላን ወደ አዲስ አበባ መመለሱን ገልጿል።
በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታን እና ግድም ወረዳ ማጀቴ ከተማ የሚኖሩ አንድ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው ድንገተኛ አደጋ አጋጥሞት ለተሻለ ህክምና ወደ ደሴ ሆስፒታል ሪፈር የተባለ ልጃቸውን ለማሳከም ብዙ ስቃይ እንዳጋጠማቸው ነግረውናል።
ትራንስፖርት በመከልከሉ ምክንያት ገጠር ገጠሩን ባሉ ቀበሌዎች ባጃጅ ኮንትራት በመያዝ ለቀናት ተጉዘው ደሴ ሆስፒታል ሙድረሳቸውን፣ በጉዟቸው ወቅት ልጃቸው ለከፋ እንግልት እሳቸው ደግሞ ለተጋነነ ወጪ መዳረጋቸውን ጠቅሰዋል።
የሰሜን ሸዋ ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ብርጋዴር ጀነራል አበባው ሰይድ "መንገዱ የተዘጋው ጽንፈኞችን ለማጽዳት ነው፣ አሁን ስራችንን እየሰራን ነው" ያሉ ሲሆን መንገዱ መቼ ይከፈታል? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን ስር ያሉ እና መንገዱ የተዘጋባቸው አካባቢዎች በመሀል ሜዳ በኩል እየተጓጓዙ ሲሆን የትራንስፖርት ዋጋ ከእጥፍ በላይ መጨመሩን ታዝበናል።
እንዲሁም በኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን፣ ደቡብ ወሎ እና ሌሎች የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት እንዲሁም ከአዲስ አበባ ለመሄድ በተለይም የአውሮፕላን ቲኬት መግዛት ያልቻሉ ሰዎች በአፋር ክልል አዋሽ በኩል አድርገው ለመጓዝ መገደዳቸውንም ሰምተናል።
በተጠቀሱት አካባቢዎች የሚጓዙ መንገደኞች መንገዱ ከተዘጋበት ጊዜ ጀምሮ የትራንስፖርት ዋጋ አንድ ሺህ ብር እና በላይ ጭማሪ ተደርጎባቸዋል ተብሏል።
በአማራ ክልል እና እንደአስፈለጊነቱ በሌሎች አካባቢዎች ተፈጻሚ እንዲሆን ባለፈው አመት ሀምሌ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ባለፈው ጥር መጨረሻ ነበር ለአራት ወራት የተራዘመው።
መንግስት አዋጁን ለተጨማሪ አራት ወራት ያራዘመው የቀሩ ስራዎች መኖራቸውን በመጥቀስ ነበር።
አምነተስቲ ኢንተርናሽናል መንግስት አዋጁን ተቃዋሚዎችን ዝም ለማሰኘት እና ለማሰር ተጠቅሞበታል የሚል ክስ ማቅረቡ ይታወሳል።
አዋጁ ተፈጻሚ በሆነበት ወቅት በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ግድያ እና አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ በርካታ ወንጀሎች መፈጸማቸውን የሚያሳዩ ሪፖርቶችን የሚያወጣው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንም(ኢሰመኮ) የአዋጁን መራዘም በሰብአዊ መብት ላይ ጥሩ አንድምታ የለውም በማለት ተችቶታል።