ከሱዳን በመግባት የግድቡን ግንባታ ለማደናቀፍ የሞከረ “ቅጥረኛ” ኃይል መደምሰሱ ተገለጸ
መከላከያ በወሰደው እርምጃ “50 የሽብር ቡድን አባላት መደምሰሱንና ከ70 በላይ የሚሆኑትን ማቁሰሉን” መግለጫው ጠቅሷል
መከላከያ ጥቃቱን ሊያደርሱ የነበሩት “በህወሃት የሽብር ቡድን” የተላኩ “ቅጥረኛ” ኃይሎች ናቸው ብሏል
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ “የሕዳሴውን ግድብ ግንባታ ለማደናቀፍ ከሱዳን በአልምሃል ሰርጎ ለመግባት የሞከረው የጁንታው ቅጥረኛ ሃይል” መደምሰሱን አስታውቋ።
መግለጫው መከላከያ ሰራዊት በወሰደው እርምጃ “50 የሽብር ቡድን አባላት መደምሰሱንና ከ70 በላይ የሚሆኑትን ማቁሰሉን” ጠቅሷል፡፡
የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ሃይል ኮማንድ ፖስት የኦፕሬሽን ዘርፍ አሰተባባሪ ኮ/ል ሰይፈ ኢንጊ ፣ “ቅጥረኛው የተለያዩ ፀረ ሰው እና ፀረ ተሽከርካሪ ፈንጂዎችን ለማጥመድ የሞከረ ቢሆንም መቋቋም ተስኖት ተበታትኗል” ሲሉ መናገራቸውን መግለጫው አስታውቋል።
መከላከያ በመግለጫው እንዳስታወቀው “ጣለት ሰአት ጠብቆ ለማጥቃት ቢሞክርም፤ የጠላትበን እንቅስቃሴ በንቃት ሲከታተል እንደነበረና እርምጃ ተወስዷል” ብሏል፡፡
መግለጫው መከላከያ ሰራዊት ሰርጎ የገባው ቡድን ሊጠቀምባቸው የነበሩ ቀላል እና ከባድ የቡድን መሳሪያዎች፣ ፈንጂዎች የወደሙ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጿል።
መከላከያ “ጥቃቱን ሊያደርሱ የነበሩት በህወሃት የሽብር ቡድን የላኩ ቅጥሮች ናቸው” ብሏል፡፡ ይሁን እንጂ ህወሃት ጥቃት አድጓል ለሚለው ክስ እስካሁን መልስ አልሰጠም።
በፌደራል መንግስትና የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሃት መካከል ጥቅምት ወር 2013ዓ.ም የተጀመረው ግጭት 11 ወራትን አስቆጥሯል።
የፌደራል መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ፤ መከላከያ ሰራዊትን ከትግራይ ክልል ካስወጣ በኋላ የህወሃት ኃይሎች የክልሉን ዋና ከተማ መቀሌን ጨምሮ ሙሉ ትግራይ መቆጣጠር ቻሉ።
የህወሃት ሃይሎች ከትግራይ አልፈው በአማራና አፋር ክልል ጥቃት በመክፈት የተወሰኑ ቦታዎችን መቆጣጠራቸው ይታወቃል። አሁን ላይ ጦርነቱ እየካሄደ ያለው በአማራ አፋር ክልል ውስጥ ሆኗል።
የፌደራል መንግስትም የተናጠል ተኩስ አቁም የተፈለገውን ለውጥ አላመጠም በማለት መከላከያና የክልል ልዩ ሃይሎች እርምጃ እንዲወስዱ ትእዛዝ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ መንግስት ህወሃት በወረራቸው አካባቢዎች ግድያና መጠነ ሰፊ ዘረፋ ፈጽሟል በማለት ይከሳል።
በመንግስት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሃት ግን በሁለቱ ክልሎች ጥቃት መፈጸሙን አምኖ፤ በንጹሃን ላይ ጥቃት አድርሷል የሚለውን ክስ እያስተባበለ ይገኛል።