ፖለቲካ
በእስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ከፍተኛ አመራሮች የእጩነት ማረጋገጫ ተሰጣቸው
ቦርዱ እጩዎቹን እንደገና ለመመዝገብ ተጨማሪ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ማውጣቱን ማስታወቁ የሚታወስ ነው
እስክንድርን ጨምሮ 4 የፓርቲው አመራሮች ማረጋገጫውን አግኝተዋል
በእስር ላይ የሚገኙት ከፍተኛ አመራሮቹ የእጩነት ማረጋገጫ ሰነድ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደተሰጣቸው የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አስታወቀ፡፡
ፓርቲው በይፋዊ የማህበራዊ ገጹ ባሰፈረው መረጃ የፓርቲውን ፕሬዝዳንት እስክንድር ነጋን ጨምሮ በእስር ላይ የሚገኙት የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች አስቴር ስዩም፣ ስንታየሁ ቸኮል እና አስካለ ደምሌ የዕጩነት የማረጋገጫ ሰነድ አግኝተዋል፡፡
ቦርዱ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በወሰነው መሰረት በእስር ላይ የሚገኙት የፓርቲውን ከፍተኛ አመራሮች በዕጩነት እንደሚመዘግብ ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡
ትናንት ከነበረው የፍርድ ችሎት ቀርበው ስለ ጉዳዩ ያብራሩት የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ተቋማቸው የፍርድ ቤት ትዕዛዝ የመፈጸም ችግር እንደሌለበት አስረድተው፤ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተጨማሪ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በማውጣት በማስፈጸም ላይ መሆናቸውን አስታውቀው ነበር።
ወ/ሪት ብርቱካን ቦርዱ የእጩነት ማረጋገጫ ሰነዱን ዛሬ አርብ ግንቦት 27 ቀን 2013 ዓ.ም ለለዕጩዎቹ እንደሚሰጥም ነበር የገለጹት፡፡
በተናገሩት መሰረትም ማረጋገጫ ሰነዱን መስጠታቸውን ፓርቲው አስታውቋል፡፡