ብራዚል አሜሪካን ተቃዋሚ መሆን አያስፈልግም ብላለች
የብሪክስ አባላት መሪዎች ማክሰኞ በጆሀንስበርግ በጀመሩት ጉባኤ የቡድኑን ቀጣይ መንገድ ለመወሰን እየተሟገቱ ነው።
በዚህም መሪዎቹ አምስት አባላት ያለውን ቡድን ማስፋፋት ላይ ልዩነት ማሳየታቸው ተነግሯል።
በዩክሬን ጦርነት ያለው ውጥረትና የቻይናና የአሜሪካ ፍጥጫ፤ ሞስኮና ቤጂንግ ከብሪክ አባላት ጠንካራ ድጋፍ ፈልገዋል።
ሁለቱ ሀገራት ማክሰኞ ተጀምሮ ሀሙስ በሚጠናቀቀው ጉባኤ የምዕራባውያን የዓለም የበላይነትን ለመቀልበስና ለመገዳደር ጫና ያደርጋሉ ተብሏል።
የቻይና ፕሬዝዳንት ዢ ቺፒንግ በንግድ ሚንስትራቸው በኩል "የታሪክ ጉዞ እኛ በምንወስነው ውሳኔ ይገራል" ብለዋል።
የብራዚሉ ሉላ በበኩላቸው በቡድኑ ውስጥ የእይታ ልዩነት እንዳለ የሚጠቁም አስተያየት ሰንዝረዋል።
የፖለቲካ ተንታኞች ሉላ በ"ዓለም አቀፉ ስርዓት" ውስጥ ወጥ የሆነ ሚና ለማግኘት ለረጅም ጊዜ እየታገሉ ነው ብለዋቸዋል።
ሉላ "ለቡድን 7፣ ቡድን 20 ወይም አሜሪካን ተቃዋሚ መሆን አንፈልግም" ብለዋል ።
"ራሳችንን ማደራጀት ብቻ ነው የምንፈልገው" በማለት አክለዋል።
ከማስፋፋት ጥያቄ ባሻገር የአሜሪካን ዶላር ጥገኝነት ለመቀነስ የአባል ሀገራቱን ገንዘቦች በንግድ እና ግብይት ላይ ማሳደግም የጉባኤው አጀንዳ ነው።