የምታውቋቸውን ሰዎች በስም አልያም በመልካቸው ለመለየት ይቸገራሉ?
ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ያደረገው ጥናት ከአለማችን ህዝብ 5 ከመቶው የቅርብ ወዳጁን ወይም ጉደኛውን በመልኩ መለየት ይሳነዋል ብሏል
ሰዎችን በመልካቸው የመለየት ችግር ስም ከመዘንጋት አባዜው እየባሰ መሄዱም ተነግሯል
የምናውቀውን ዘመድ ወይ ጓደኛ ስም የመዘንጋት ችግር በብዙዎቻችን ላይ ይታያል።
“አፌ ላይ እኮ አለ” ብለን ለሰከንዶች እና ደቂቃዎች አስበንም የማይሳካልን ጥቂቶች አይደለንም።
የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ያወጣው አዲስ ጥናት ደግሞ የሰዎችን መልክ የመለየት ችግር (ፌስ ብላይንድነስ) ስምን ከመዘንጋቱ በባስ ብዙዎች የሚጋሩት ባህሪ ሆኗል ይላል።
የቅርብ ሰዎቻችን የነበሩ አልያም ጓደኞቻችን ረዘም ካለ ጊዜ በኋላ መንገድ ላይ ስናያቸው “የት ነው የማውቀው? እክሌ ነው? አይ አይደለም ” በሚሉና ሌሎች አወዛጋቢ ጥያቄና መልሶች ከተጠመድን በ“ፕሮሶፓግኖሲያ” ተጠቅተናል ማለት ነው።
አሜሪካዊው የፊልም ተዋናይ ብራድ ፒት ባለፈው አመት በዚህ ችግር ተጠቅቶ ቤተሰቦቹን ጭምር መለየት ተስኖት እንደነበር ሲገልጽ መነጋገሪያ መሆኑን ይታወሳል።
በብሪታንያ የከፋ መልክን የመለየት ችግር ያለባት ሃናህ ሬድ የተባለችው እንስትም፥ “እያንዳንዱ ሰው ለእኔ ተመሳሳይ ነው፤ ሁለት አይን፣ አንድ አፍንጫ እና አንድ አፍ አለው፤ አይለያይም” ትላለች።
እንደ ሃናህ ያሉ ከባድ ፈተና ውስጥ ያሉ ሰዎች፥ የቅርቦቻቸውን ሰዎች በአረማመዳቸው፣ በድምጻቸው፣ በልብስ ምርጫቸው እና የጸጉር አቆራረጣቸው ሊለዩዋቸው ወይም ሊያስታውሷቸው ይችላሉ።
ከዚህ ቀደም የተደረጉ ጥናቶች ከ2 እስከ 2 ነጥብ 5 በመቶ የአለማችን ህዝብ ፊትን ወይም መልክን የመለየት ችግር እንዳለበት ማረጋገጣቸውን ዴይሊ ሜል አስታውሷል።
ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ ከ3 ሺህ 300 በላይ ሰዎች ላይ ያደረገው ጥናት ግን የተጠቂዎቹን ቁጥር ወደ 5 ነጥብ 4 በመቶ ከፍ ማለቱን አመላክቷል ነው ያለው ዘገባው።
በሶስት ደረጃ (እጅግ ከባድ፣ መካከለኛ እና መጠነኛ) ተብሎ የተከፈለው የሰዎችን መልክ በፍጥነት የመለየት ችግር በስትሮክ ወይንም በጭንቅላት ላይ በሚደርስ አደጋ የሚከሰት ነው በአንዳንድ ሰዎች ላይም በዘር ውርስ ይተላለፋል ይላል ጥናቱ።
የለንደን ኪንግ ኮሌጅ ተመራማሪዎች መሰል ችግር ውስጥ እንዳሉ የሚጠራጠሩ ሰዎች እንዲሞሉትና ደረጃቸውን እንዲለዩ 20 ጥያቄዎችን የያዘ መጠይቅ አዘጋጅተዋል።
ከጥያቄዎቹ ውስጥ “ከቤተሰቦችህ ውስጥ ወይም የቅርብ ጓደኛህን መልክ መለየት ተቸግረህ ታውቃለህ?”፣
“በልጅነትህ የክፍል ጓደኞችህን ለመለየት ትቸገር ነበር?”፣
“ተዋናዮቹን መለየት ስለሚከብድህ ፊልም ማየት አትወድም?” ፣
“ሰዎች አለባበሳቸውን ወይም የጸጉር አሰራራቸውን ሲለውጡ መለየት ይከብድሃል?” የሚሉት ይገኙበታል።
ለእያንዳንዱ ጥያቄዎች ከአምስት ነጥብ የሚሰጥ ሲሆን፥ ከ100 ያገኘነው ውጤት ያለንበትን ሁኔታ ያሳያል ብለዋል ተመራማሪዎች።
የሰዎችን መልክ በፍጥነት የመለየት ችግርን ለመቀነስ ህክምና አለ ቢባልም፥ የማስታወስ ችሎታን የሚጨምሩ ምግቦችን መመገብ ወሳኝ ድርሻ እንዳለው ተነግሯል።
ከፊት ገጽ መለያ ውጭ ያሉ የሰዎች አረማመድ፣ አነጋገርና አለባበስ ላይ ትኩረት ማድረግም ሌላው መፍትሄ ነው ተብሏል።