የታገቱት ተማሪዎች “ዶክመንታቸው ተገኝቷል”፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማገት የተጠረጠሩ “በርካታ ሰዎቸ በቁጥጥር ስር” መዋላቸውን ገልጸዋል
ምርመራ እየተካሄደ ነው“ምናልባት ፍንጭ ይገኝ ይሆናል፤ወይም የበላቸው ጅብ ይጮሃል”፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ
ምርመራ እየተካሄደ ነው“ምናልባት ፍንጭ ይገኝ ይሆናል፤ወይም የበላቸው ጅብ ይጮሃል”፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ
ከወራት በፊት ከደንቢዶሉ ዩኒቨርሲቲ ወጥተው ወደ ቤታቸው በመሄድ ላይ ሳሉ ታግተው ደብዛቸው የጠፋው ተማሪዎች “ዶክመንታቸው” [የትምህርት ማስረጃቸው] መገኘቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህን ያሉት በዛሬው እለት በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት በቀረቡበት ወቅት አንድ የምክርቤቱ አባል የታገቱት ተማሪዎች በምን ሁኔታ ላይ ናቸው? ብለው ላነሱት ጥያቄ መልስ በሰጡበት ወቅት ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “የመከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስ ብዙ አሰሳዎችንና ዘመቻዎችን አካሂዷል፤ ብዙ ሀብት ባክኗል፡፡ ተማሪዎቹ አሉባቸው በተባሉባቸው ሁሉም ቀበሌዎች አሰሳ ተደርጓል፤ የሞተ ሰው አንድም አልተገኘም፡፡ለእገታው ኃላፊነቱን የምወስድው እኔ ነኝ ብሎ የወጣ አንድም አካል የለም”
እስካሁን በተካሄደው ጥረት “ጠለፋውን ያስተባበሩ፤ ያቀነባበሩና ያሳለጡ በርካታ ሰዎቸ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ለምስሌ ታግቼ ነበር ብላ የነበረችው ልጅ የሷን ዶክመንትና የሌሎችን ተማሪዎች ዶክምንት የያዘው ሰው ተይዟል፡፡ ተገኝቷል ዶክመንቸው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በቴክኒክ መረጃ የአንዳንዶቹ ታጋቾች ስልክ አማራ ክልል ይገኛል፤ አማራ ክልል ሲፈለግ ስልኩ ጠፍቶ ቤንሻንጉል ክልል ይገኛል ፤ ቤንሻንጉል ሲፈለግ ኦሮሚያ ክልል ይገኛል፡፡ እንቅስቃሴ አለ”
“ትንሽ ተራ እገታ ብሎ ለማመን” እንደሚያስቸግር የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት ተማሪዎቹን ለማግኘት “በጊዜም፣ በገንዘብም በወታደርም ምንም የሰሰተው ነገር የለም” ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማገት የተጠረጠሩ“አሁን በርከት ያሉ ሰዎች ተይዘው ምርመራ እየተደረገ ነው፤ ምናልባት ፍንጭ ይገኝ ይሆናል፤ወይ የበላቸው ጅብ ይጮሃል፡፡ በኛ በኩል ልጆቹን ለመታደግ ጥረት ሳናደርግ ቀርተን አይደለም፡፡”
“አሁን ታግቼ ነበር ብለው በተለያዩ ከተማ የምንይዛቸው ሰዎቸ የታገቱ አይደሉም፡፡ ይህ መንግስትን የታገቱትን ያዝኩ ሲል የፖለቲካ ጨዋታ ለመጫወት ነው፡፡ ብዙ ድራማ ሚሰራበት ስለሆነ እኛም የምንችለውን እናደርጋለን፡፡ ጊዜ ይመልሰዋል “ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
“ይሄ የእውር ድንብር ፍላጋ ነው፡፡ያገተው አይታወቅም ማሰስ ነው፡፡ ጉዳዩን ከቤተሰብ ጉዳይ ውጭ አድርገው የፖለቲካ አጀንዳም ለማድረግ የሚፈልጉ አካለት አሉ” በማለት ጠቅላይ ሚኒስተሩ የጉዳዩን ውስብስነት ገልጸዋል፡፡
የተማሪዎቹ መታገት ከተሰማ በኋላ ተማሪዎቹ የት ሄዱ የሚል አንዴ ሞቅ፣ አንዴ ደግሞ ቀዝቀዝ የሚል ዘመቻ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡