“ኢትዮጵያና ሱዳን ወደ ግጭት ሚገቡበት ምንም ምክንያት የለም” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር አካባቢ ከቀናት በፊት ግጭት መከሰቱ ይታወቃል
ሰሞኑን በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር የተፈጠረው ክስተት የሁለቱን ሀገራት ጠንካራ ግንኙነት አይወክልም ተባለ
“ኢትዮጵያና ሱዳን ወደ ግጭት ሚገቡበት ምንም ምክንያት የለም” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
ከሰሞኑ ኢትዮጵያና ሱዳን በሚዋሰኑበት ድንበር አካባቢ የተፈጠረው አለመግባባትና ግጭት በውይይት እንደሚፈታ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ሚኒስቴሩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አላስፈላጊ ውጥረትን በማስወገድ ሁለቱ ሀገራት ከዚህ በፊት ባስቀመጧቸው የግጭት አፈታት ስልቶች መፈታት እንዳለበት አስታውቋል፡፡ ሁለቱን ሀገራት ወደ ግጭት ውስጥ የሚያስገባ ምንም አይነት ምክንያት እንደሌለ የገለጸው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳ ሚኒስቴር በሁለቱ ሀገራት አጎራባች አካባቢዎች መካከል ያለው ትብብር እንዲጠናከር በማድረግ መሰል ግጭቶችን በአጭር መቅጨት ያስፈልጋል ብሏል፡፡
ሰሞነኛው ግጭት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ጠንካራ ግንኙነት የማይወክል መሆኑን የገለጸው ሚኒስቴሩ ይህንንም በውይይት መፍታት እንደሚገባ ገልጿል፡፡ ከማክሰኞ ዕለት ጀምሮ ኢትዮጵያና ሱዳን በሚዋሰኑበት ድንበር ላይ አለመግባባት መቀስቀሱን ተከትሎ ነው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ መግለጫ የሰጠው፡፡
ሁለቱ ሀገራት ወደ ጠላትነት የሚወርዱበት ምንም ምክንያት እንደሌለ በመግለጽ በአጎራባች የአካባቢ እና የክልል አስተዳደሮች መካከል የተቀናጀ ት ብብር ቀጣይነት እንዲኖረው ጥሪውን አስተላል ፏል፡፡ እንደነዚህ ያሉት ክስተቶች በተሻለ ሁኔታ መፍትሔ የሚያገኙት በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለው መልካም እና ወዳጃዊ እንዲሁም ሰላማዊ ግንኙነት ላይ በመመርኮዝ እንደሆነም ገልጿል፡፡ ይህ ክስተት በሁለቱ አገራት ህዝቦች መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት የሚወክል እንዳልሆነም ነው ጠውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያብራራው፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል መልካም ግንኙነትን እና መግባባትን መሠረት ያደረጉ የረጅም ጊዜ ግንኙነቶችን የሚያንፀባርቅ ጠንካራና ወዳጃዊ አከባቢን የበለጠ ማጎልበት አስፈላጊ መሆኑንም አውስቷል የሚኒስቴሩ መግለጫ፡፡
የሱዳን ጦር ቃል አቀባይ አሚን መሐመድ ሐሰን (ዶ/ር) ከሰሞኑ ግንቦት 18 ቀን 2012 ዓ.ም “የኢትዮጵያ ታጣቂዎች” አትባራ ወንዝ ውሃ ሊቀዱ መምጣታቸውንና ከሱዳን ወታደሮች ጋር አለመግባባት ተፈጥሮ እንደነበርና ይህም ወደ ግጭት ማምራቱን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
አሚን መሐመድ ሐሰን (ዶ/ር)
የሱዳን ወታደሮች “የኢትዮጵያን ታጣቂዎች” ውኃ አትወስዱም በማለታቸው አለመግባባቱ ወደ ግጭት ማምታቱን አስታውቀዋል፡፡ የሱዳን ጦር እንደገለጸው በተፈጠረው ግጭት የሰው ህይወት አልፏል፡፡
ከሰሞኑ በካርቱም በተሰጠው መግለጫ የሱዳን ጦር ቃል አቀባይ ዶ/ር አሚን መሐመድ ሐሰን በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ በከባድ መሳሪያ የታገዘ ውጊያው እንደነበር ገልጸው በዚህም አንድ ኮማንደርና ከስድስት ወታደሮች እንዲሁም አንድ ህጻንና ሌላ ሰላማዊ ሰው ህይወታቸው ማለፉን አስታውቀው ነበር፡፡
የሱዳን ዜና አገልግሎት ወደ አካባቢው ሱዳን ተጨማሪ ኃይል መላኩንና ታጣቂ ያለቸሰቸውንም ከሱዳን ግዛት እንዲወጡ ማድረጓን ቢዘግብም ኢትዮጵያ ጉዳዩ በውይይት እንደሚፈታ ገልጻለች፡፡ ከዚህ ባለፈም በድንበር አካባቢው ምን እንደተፈጠረ የማጣራት ስራ እንደሚሰራም ገልጻለች፡፡ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሰሞኑ በሁለቱ ሀገራቱ ድንበር ላይ በተከሰተው ግጭት ለተጎዱት የሁለቱም ሀገራት ዜጎች ሀዘኑን ገልጿል፡፡