በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ኬንያ ከግብፅ ጎን ቆማለች በሚል የሚሰራጨው መረጃ ሀሰት እና የግብፅ የተለመደ ፕሮፓጋንዳ ነው።" አምባሳደር መለስ አለም
በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ኬንያ ከግብፅ ጎን ቆማለች በሚል የሚሰራጨው መረጃ ሀሰት እና የግብፅ የተለመደ ፕሮፓጋንዳ ነው።" አምባሳደር መለስ አለም
በግብጹ አል አህራም ጋዜጣና በተለያዩ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የኬንያ መንግስት በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ግብፅን እንደደገፈ ተደርጎ የተሰራጨው ዜና ፍጹም ውሸትና ከዚህ ቀደምም የሚደረግ የተለመደ ማደናገሪያ መንገድ ነው ሲሉ በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ አለም ገለጹ፡፡
አምባሳደሩ ጉዳዩን በተመለከተ ከአል ዐይን ጋር ቆይታ ያደረጉ ሲሆን በግብጹ ሚዲያ ኬንያ ከግብጽ ጎን ቆመች የሚለው ውሸት መሆኑን ለማረጋገጥ በኬንያ ቤተ መንግስት (state house) የፌስቡክ ገጽ ላይ ያለውን መረጃ ማየት በቂ ነው ብለዋል፡፡
አህራም ጋዜጣ የግብጽን አንድ የስራ ኃላፊ ጠቅሶ ትናንት ባወጣው ጽሁፉ ፕሬዝዳን ኡሁሩ ኬኒያታ “የግብፅ አቋም ‹ከቅን ፍላጎት› የመነጨ ነው” ሲሉ ተናግረዋል ያለ ቢሆንም፣ የመረጃውን ሀሰትነት ለማስረዳት አምባሳደር መለስ የግብፅ ሚዲያዎች ከቀናት በፊት ጥቂት ግብፃውያን የተሰበሰቡበት ፎቶ በመለጠፍ በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ግብፅን ደገፉ በሚል የሀሰት ዜና ማሰራጨታቸውን በዋቢነት አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በናይሮቢ በነበራቸው ጉብኝት ከኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ፕሬዝዳንቱ የአፍሪካውያን አለመግባባቶች በአፍሪካውያን መፈታት እንዳለባቸው የሚያምኑበት መሆኑን አረጋግጠውላቸዋል ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳት ኡሁሩ ኬንያታ ይህንን ማለታቸውም በፕሬዝዳንቱ የፌስቡክ ገፅ ላይ እንደሚገኝ አምባሳደር መለስ አለም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ ያላትን አቋም ለማስረዳት ባለፉት ሁለት ሳምንታት የልዑካን ቡድኖችን ወደ ተለያዩ ሃገራት የላከች ሲሆን ቡድኑ ከተላከባቸው ቦታዎች አንዷ ኬንያ ነች፡፡
በንግግራቸው ላይም የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የዓባይን ወንዝ በተመለከተ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ ክፍፍል መኖር አለበት ማለታቸው ይታወሳል፡፡