የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች አመራሮች በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የአሜሪካና የዓረብ ሊግን ውሳኔ አወገዙ
የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች አመራሮች በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የአሜሪካና የዓረብ ሊግን ውሳኔ አወገዙ
የኢትዮጵያ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የምክክር መድረክ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ የካቲት 28 ቀን 2012 ዓ/ም
ወቅታዊ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡
የዩኒቨርሲቲዎቹ ፕሬዜዳንቶች እና ምክትል ፕሬዜዳንቶች በግድቡ ዙሪያ ውይይት አድርገው፣ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ኢፍትሃዊ የሆነ ውሳኔ ለመወሰንና ለማስወሰን እንዳንድ ሀገራት የተዛባ ውሳኔ እንዲሰጥ ጫና ለመፍጠር እየጣሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደምም ከቅኝ ገዥ ወራሪዎች ጋር በተያያዘ እ.አ.አ በ1949 በ ሊግ ኦቭ ኔሽንስ (League of Nations) ተመሳሳይ የተዛባ ውሳኔ ሲተላለፍ የወቅቱ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አክሊሉ ሀብተወልድ የተናገሩትን ያስታወሰው መግለጫው፣ ኢትዮጵያ ዛሬም ሆነ ነገ ነፃነቷን ለመጠበቅና ታሪኳን ለማስከበር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ አለባት ይላል፡፡
አክሊሉ ሀብተወልድ በወቅቱየሚከተለውን ብለው ነበር፡፡ ‹‹ሀገሬ ኢትዮጵያ በአለም ሸንጎ ላይ ፍርድ ተነፍጓት ስታዝን የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም፡፡ ለነፃነቷና ለመብቷ ከኮሎኒያልስት ጣሊያን ጋር በየጊዜው ስትዋጋ ያሸነፈችውም ብቻዋን ነው፡፡ የተጠቃችውም ብቻዋን ስለሆነ ሀገሬ መቼውንም በሚደርስባት አደጋ ከማንም እርዳታ አገኛለሁ ብላ አትጠብቅም፡፡››
የአክሊሉ ሀብተወልድ እንዳሉት ‹‹አሁንም ያለን ትውልዶች የተዛባውን ሚዛን ማስተካከል ያለብን እኛው ነን፤ የአድዋውን ድል በተባበረው በአያቶቻችን ክንድ እዳሸነፍነው ሁሉ የህዳሴውንም ግድብ በተባበረው አንድነታችን፣ ክንዳችን እና ሀብታችን ሰርተን የምንጨርሰው መሆናችንን እናረጋግጣለን›› ይላል መግለጫው፡፡
የግድቡ መገንባት በሀገሪቱ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ የጎላ ድርሻ ያለው ሲሆን ኮሎኒያሊስቶች አፍረካን እና ሀብቷን ለመቀራመት አውጥተውት በነበረውና አሁን በሚያፍሩበት (ኢትዮጵያ ባልተወከለችበት) ሕግ ተገዥ የምትሆንበት ሕጋዊም ሆነ አመክኒያዊ ምክኒያት እንደሌለ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች የምክክር መድረክ ተሳታፊዎች ከዚህ በላይ በቀረበው መነሻነት ከታች የተዘረዘሩትን ባለ ስድስት ነጠብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡
1ኛ/ የጀመርነውን እውን ለማድረግ ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደምናደርግ እናረጋግጣለን፡፡
2ኛ/ የህዳሴው ግድብ የአንድነታችን ተምሣሌት በመሆኑ በዘር፣ በኃይማኖትና በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳይኖር የመንግስትን አቋም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲደግፍ እንጠይቃለን፡፡
3ኛ/ እኛ ጠግበን በብርሃን እየኖርን እናንተ በርሃብና በጨለማ ኑሩ የሚል ራስ ወዳድ አስተሳሰብን በፅኑ እናወግዛለን፡፡
4ኛ/ እኛ የኢትዮጵያ የመንግስት ዩኒቨርስቲ አመራሮች በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውን የየድርሻቸውን እንዲወጡና ዲፕሎማሲያዊ ጫና እንደያሳድሩ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
5ኛ/ የዓረብ ሊግ በኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ሰሞኑን የወሰነውን ኢ-ፍትሐዊ ውሳኔ እየተቃወምን የአፍሪካ ህብረት እንዲህ ዓይነት ጣልቃ ገብነትን እንዲቃወምና መርህን እና ሕግን መሠረት በማድረግ ከኢትዮጵያ ጐን እንዲቆም እንጠይቃለን፡፡
6ኛ/ የአሜሪካ መንግስት በታዛቢነት ገብቶ ሀብት እና ዲፕሎማሲያዊ ኃይሉን በመጠቀም ወደ አደራዳሪነት እራሱን ከማሸጋገር በላይ የወሣኝነት ሚና ያለው የሚመስል መግለጫ ማውጣቱን አጥብቀን እንቃወማለን፡፡
ምንጭ፡- አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ