ግድቡ “የሱዳንን ብሔራዊ ጥቅም” የሚያስጠብቅ ነው-ሱዳን
ጄነራል ብርሃኑ ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጋር በካርቱም በተወያዩበት ወቅት ሱዳን ይህን አቋሟን ገልፃለች
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ “የሱዳንን ብሔራዊ ጥቅም” እደሚያስጠብቅ ሱዳን አስታውቃለች
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ “የሱዳንን ብሔራዊ ጥቅም” እደሚያስጠብቅ ሱዳን አስታውቃለች
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ “የሱዳንን ብሔራዊ ጥቅም” የሚያስጠብቅ በመሆኑ ሱዳን ድጋፍ እሰጣለሁ ማለቷን በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አሰታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ጦር ሃይሎች ምክትል የኢታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጋር በካርቱም በተወያዩበት ወቅት ነው ሱዳን ይህንን አቋም ማንጸባረቋን ኤምባሲው የገለጸው፡፡
በጄነራል ብርሃኑ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ ከሰሞኑ በጠቅላይ ሚኒስተር ሃምዶክ ላይ የተቃጣውን የግድያ ሙከራ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተላከ መልዕክትን ማድረሳቸውም ታውቋል።
የልዑክ ቡድኑ ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ በተጨማሪም ከሱዳኑ መከላከያ ሚኒስትር ጄነራል ጀማለዲን ኦማር እና ከሱዳን ኤታማዦር ሹም ጄነራል ኡስማን መሃመድ ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
ጄነራል ብርሀኑ በቅርቡ በሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ የተቃጣው የግድያ ሙከራ ያወገዙ ሲሆን ኢትዮጵያ እንዲህ ባለው አስቸጋሪ ሁኔታ ከሱዳን ጎን እንደምትቆም አረጋግጠዋል፡፡
በቅርቡ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በአሜሪካ ሲያካሂዱት የነበረውን ድርድር ያለስምምነት ማጠናቀቃቸው የሚታወስ ነው፡፡ ድርድሩ ያለስምምነት የተጠናቀቀው ሶስቱ ሀገራት ይፈርሙታል የተባለውን የመጨረሻውን የስምምነት ሰነድ፣ ኢትዮጵያ አልፍርምም፤ ተጨማሪ ጊዜ ወስጄ በጉዳዩ ላይ ብሄራዊ ውይይት ማድረግ እፈልጋለሁ በማለት ወደ አሜሪካ ባለማቅናቷ ነው፡፡
ኢትዮጵያ፣ በግብፅ ጥያቄ መሰረት በግድቡ ድርድር ላይ ታዛቢ የሆነችው አሜሪካ ሚናዋ ከታዛቢነት ወደ አደራዳሪነት፣ ከአደራዳሪነት ወደ ሰነድ አርቃቂነት በመቀየሩ የድርድሩ መንፈስ ተገቢ አይደለም ብላ ተቃውሞዋን አሰምታለች፡፡
ግብጽ በአንፃሩ ስምምነቱን የፈረመች ሲሆን ኢትዮጵያ ባለመፈረሟ ትችት ሰንዝራለች፡፡ግብጽ ከትችት ባለፈም ኢትዮጵያን የሚኮንን የስምምነት ሰነድ በማዘጋጀት በአረብ ሊቅ እንዲያጸድቅ አድርጋለች፡፡
ሱዳን በበኩሏ የአረብ ሊግን አቋም በጽኑ መቃወሟ ይታወሳል፡፡