ለኢዴፓ “ከምርጫ 2012” በኋላ የታዩት መጥፎ ቢሆኖች
“ገዥው ፓርቲ በለመደው እንቢተኝነት” ምርጫውን የሚያካሂደው ከሆነ ሊከሰቱ የሚችሉ መጥፎ ግምቶቹን ኢዴፓ አስቀምጧል
ኢዴፓ ምርጫው የሚካሄድ ከሆነ ይመጣሉ ያላቸውን መጥፎ ቢሆኖችን በሰነድ ዘርዝሯቸዋል
ኢዴፓ ምርጫው የሚካሄድ ከሆነ ይመጣሉ ያላቸውን መጥፎ ቢሆኖችን በሰነድ ዘርዝሯቸዋል
ከምርጫ በፊት የሽግግር መንግስት መመስረት አለበት በሚል አቋሙ የሚታወቀው የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፤ ምርጫው የሚካሄድ ከሆነ ሀገሪቱ ችግር ውስጥ ልትገባ የምትችልበትን ግምቶች ሰንዷል፡፡
ፓርቲው ዛሬ ይፋ ባደረገውና 25 ገጽ ባለው “ህዳሴ የእርቅና የአንድነት የሽግግር መንግስት“ በተሰኘው ሰነድ ላይ “ገዥው ፓርቲ በተለመደው እንቢተኝነት” ምርጫውን የሚያካሂደው ከሆነ፣ ከምርጫ በኋላ ሊመጡ የሚችሉ ጥሩና መጥፎ ቢሆኖችን(Scenarios)በዝርዝር አስቀምጧል፡፡
የፓርቲው የመጀመሪያው ግምት “ምርጫው ተካሂዶ በአንጻራዊት ሰላማዊ፣ ነጻና ፍትሀዊ ሆኖ ይጠናቀቃል” የሚል ሲሆን “ይህ የሚሆን ከሆነ የኛ ግምት ስህተት ይሆናል” በዚህም ፓርቲው ደስተኛ ይሆናል ብሏል ሰነዱ፡፡
ፓርቲው በሰነዱ ላይ ምርጫው ከተካሄደ መጥፎ ግምቶች ብሎ ያስቀመጣቸው ደግሞ “ምርጫ ተካሂዶ ግጭት አፈናና ማጭበርበር የተሞላበት ይሆናል፤ ’“የወቅቱ የለውጥ”’ ኃይልም የለየለት አምባገነን ሆኖ ስልጣን ላይ ይቆያል፤ ይህ ከሆነ ግምታችን ትክክል ነበር ማለት ነው::”
ከዚህ በተጨማሪም ከምርጫ እለት በፊት በሚፈጠር ከአቅም በላይ በሆነ ብጥብጥ ምርጫው ሊቋረጥ ይችላል፤ ምርጫው ከተካሄደ በኋለም የምርጫውን ውጤት ባለመቀበል ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ ሆነው ሀገሪቱ ወደ እርስበስርስ ጦርነት ወይንም መንግስት የለሽ ሁኔታ ይገባል” ብሎ ፓርቲው ስጋቱን ገልጿል፡፡
ሰነዱ ኢዴፓ ቢቋቋም ያለው የ“ህዳሴ የእርቅና የአንድነት የሽግግር መንግስት“ መዋቅር ምን መምሰል እንዳለበት በዝርዝር አስቀምጧል፡፡
በሰኑዱ ላይ ፓርቲው ከህዝብ ጋር ከተወያየ በኋላ ጸድቆ ኦፊሴላዊ ሰነድ እንደሚሆን ፓርቲው አስታውቋል፡፡
መንግስት ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እንደሚካሄድ ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድም በበኩሉ ምርጫው ነሀሴ 23 እንደሚካሄድና ለዚህም አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጀት እያካሄደ መሆኑን አስታውቋል፡፡