የቴክኒክ ባለሙያዎች ሳይንሳዊ ትንታኔ የናይል ተፋሰስ የትብብር መሠረት መሆን እንዳለበት ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ተናገሩ፡፡
የቴክኒክ ባለሙያዎች ሳይንሳዊ ትንታኔ የናይል ተፋሰስ የትብብር መሠረት መሆን እንዳለበት ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ተናገሩ፡፡
ከትናንት በስቲያ ሰኞ መጋቢት 07 ቀን 2012 ዓ.ም ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በሩዋንዳ ባደረጉት ጉብኝት ከሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ጋር በህዳሴ ግድቡ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በኪጋሊ ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ፕሬዝዳንት ካጋሜ እንዳሉት፣ በናይል ተፋሰስ ሀገራት መካከል የሚደረግ ትብብር በቴክኒክ ባለሙያዎች የተዘጋጁ ሳይንሳዊ ትንታኔዎችን ማእከል ያደረገ መሆን አለበት፡፡
“ግብጽ ናይልን የህልውና ጉዳይ አድርጋ እንደምታስበው ሁሉ፣ የተፋሰሱ ሀገራት በውሀው ለመጠቀም ያላቸውን ተፈጥሯዊ መብትም ልታከብር ይገባል” ሲሉም ፕሬዝዳንት ካጋሜ ተናግረዋል፡፡
የናይል ጉዳይ የሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ፐሬዝዳንት ካጋሜ፣ በወንዙ ላይ የተነሱ አለመግባባቶች በአፍሪካውያን ውይይት እና ድርድር ሊፈቱ እንደሚገባ እና ሀገራቸውም የመፍትሄው አካል ለመሆን ቁርጠኛ መሆኗን አበክረው ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተፋሰሱ ሀገራት በምክንያታዊ እና ፍትሀዊ የውሀ አጠቃቀም መርህ መሰረት ወንዙን በጋራ መጠቀም አለባቸው የሚል እምነት እና አቋም እንዳላት፣ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ለፕሬዝዳንት ካጋሜ አብራርተዋል፡፡
የናይል ተፋሰስ ሀገራት የትብብር ማእቀፍ ስምምነት (CFA) ከኢትዮጵያ የትብብር አቋም የመነጨ መሆኑን በመጥቀስ፣ ኢትዮጵያ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር በቅርበት እየሰራች እንደምትገኝ ፕሬዝዳንቷ ተናግረዋል፡፡
በግድቡ ዙሪያ የተፋሰሱን ሀገራት ጥርጣሬና ስጋት ለመቅረፍ ኢትዮጵያ በየጊዜው ከግንባታው መጀመሪያ ጀምሮ በራሷ አስተባባሪነት ግልጽ ማብራሪያ እየሰጠች መምጣቷንም ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ መካከል በ2015 የተፈረመው የመርሆች መግለጫ ስምምነት ተተግብሮ የናይል ተፋሰስ የግጭት እና ያለመግባባት ምክንያት ከመሆን ይልቅ የትብብር ምንጭ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋም ፕሬዝዳንቶቹ በውይይታቸው ወቅት አንስተዋል፡፡
ምንጭ፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር