“ዱምስዴይ” አውሮፕላን ከሌሎች የጦር አውሮፕላኖች ምን የተለየ ያደርገዋል…?
“ዱምስዴይ” የሚል መጠሪያ ያለው እና የኒኩሌር የጦር መሳሪያን መቋቋም እንደሚችል የተነገረለት አውሮፕላን ሰሞኑን በሪታኒያ እንዲያርፍ ተደርጓል።
ንብረትነቱ የአሜሪካ እንደሆነ የተነገረለት አውሮፕላኑ መነሻውን ከአሜሪካው ከአንድሪው የአየር ኃይል ማዘዣ አድርጎ ወደ ብሪታኒያ ያቀናው ሩሲያ በዩክሬን እያደረገችው ባለው ዘመቻ የኒኩሌር የጦር መሳሪያ ልትጠቀም ትችላለች በሚል ስጋት እንደሆነ ተነግሯል።
“GRIM99” የሚል መለያ ኮድ ያለው አውሮፕላኑ “በራሪው ፔንታጎን” የሚል ቅጽል ስም ያለው ሲሆን፤ በኒኩሌር ጦርነት ወቅት የዘመቻዎች መዘዣ ማዕከል በመሆን ያገለግላል ተብሏል።
“ዱምስዴይ” አውሮፕላን ከሌሎች የጦር አውሮፕላኖች ምን የተለየ ያደርገዋል?
“ዱምስዴይ” የቦይንግ 747 ምርት አውሮፕላኑ ብሄራዊ የአደጋ ጊዜ የአየር ማዘዣ ማእከል በሚል ይፋዊ ስሙ የሚታወቅ ሲሆን፤ አራት መሰል አውሮፕላኖች ብቻ ናቸው ያሉት።
አራቱም አውሮፕላኖች ከፈረንጆቹ 1980 ጀምሮ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሆኑም ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።
አብዛኛው የአውሮፕላኑ ክፍል ያዘው መሳሪያ ሚስጥራዊ ነው የተባለ ሲሆን፤ የኒኩሌር አረርን መቋቋም የሚችል እና በጦርነት ወቅት በአሜሪካ ጦር አዛዥ ጋር በቀጥታ ግንኙንተ ለማድረግ የሚያስችል ነው ተብሏል።
በጦርነት ወቅትም የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትርን ለማጓጓዝ ይውላል የተባለ ሲሆን፤ አብዛኛው የአውሮፕላኑ የቅብ ስራዎች ከአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች አውሮፕላን “ኤር ፎርስ ዋን” ጋር ተመሳሳይነተ ያለው ነው።
አውሮፕላኑ በአየር ወለዶች በሰማይ ላይ እያለ ነዳጅ እየተሞላለት ያለማቋረጥ ለ150 ሰዓታት መብረር ይችላል የተባለ ሲሆን፤ አራት የጄነራል ኤሌክትሪክ ሞተሮች እና በጣም ከፍተኛ መጠን የመያዝ አቅም ያለው የነዳጅ ታንከርም ተገጥሞለታል።
67 ሳተላይት ዲሾች የተገጠሙለት አውሮፕላኑ፤ ይህም የመከላከያ ሚኒስትሩ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከሚገኙ የአሜሪካ የጦር መርከቦች፣ ሰርጓጅ መርከቦች፣ የአየር እና የመድር ጦር ኃይሎች ጋር ለመገናኘት የሚያስችላቸው ነው።
አውሮፕላኑ በአንድ ጊዜ እስከ 112 ሰዎችን መያዝ የሚችል ሲሆን፤ በውስጡ የመኝታ ክፍሎች፣ ማብሰያ ክፍል፣ የኮንፍረንስ እና የብሪፊንግ አደራሾችን ጨምሮ የዘመቻ ማዘዣ ማዕከል በውስጡ ይዟል።
አውሮፕላኑ ከመሬት በ14 ሺህ ሜት ከፍታ ላይ በሰዓት 969 ኪሎ ሜትር መብረር እንደሚችል የተነገረ ሲሆን፤ 377 ሺህ ኪሎ ግራም ጭነት ይዞ መነሳት እና ማረፍ የሚችል ነው።
ከፈረንጆቹ 1980 ጀምሮ አገልግሎት በመስጠት የጀመረው አውሮፕላኑ እስከ ፈረንጆቹ 2039 ድረስ አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል።