ሩሲያ የዩክሬንን የአየር ክልል ለመዝጋት የሚሞክር ኃይል እርምጃ ይወሰድበታል ብላለች
“ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” የሚል ተልዕኮ በመያዝ ከዩክሬን ጋር ውጊያ ውስጥ የገባችው ሩሲያ የመጀመሪያውን ምዕራፍ ማጠናቀቋን አስታወቀች።
ሞስኮ፤ በጦርነቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግቦችን እንደተሳኩላት የገለጸች ሲሆን ብዙ የዩክሬን ግዛቶችን ተቆጣጥሪያለሁ ብላለች።
የሩሲያ መከላከያ መስሪያ ቤት እንዳለው በዩክሬን ላይ የተወሰደው “ወታደራዊ ዘመቻ” የመጀመሪየው ዙር ተጠናቋል።
ሩሲያ የዩክሬንን ዋና ከተማ ኪቭን መክበቧን ባወጣችው መግለጫ አስታውቃለች። ከዚህ በተጨማሪም ካርኪቭ፣ ቼርኒሂቭመ ሱሚ እና ሚኮላይቭ የተባሉ አካባቢዎችም በሩሲያ ጦር ተከበዋል ተብሏል።
ኬርሶን እና ዛፖሮዚ የተባሉ የዩክሬን ግዛቶች አሁን ላይ በሩሲያ ጦር እጅ ላይ ወድቀዋል ተብሏል።
ሩሲያ የዩክሬንን የአየር ክልል ለመዝጋት ከሚሞክር ኃይል ጋር ጦርነት እንደምትከፍትም ገልጻለች። የሩሲያ ጦር በዩክሬን የተገንጣዮች ግዛት የሆነችውን ሉሃንስክን 93 በመቶ መቆጣጠሩን አስታውቋል።
ሩሲያ ጎረቤቷ ዩክሬን ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከፈረንጆች የካቲት 24፤ 2022 ጀምሮ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄድ መጀመሯ ይታወቃል።
አራት ሳምንታት ባስቆጠረው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ከ3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሀገራቸውን ለቀው ወደ ጎረቤት ሀገራት ለመሰደድ እንደተገደዱ ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ያወጣው ሪፖርት ያመለክታል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ እየወሰደች ያለውን ወታደራዊ እርምጃ ከጀምሩም ቢሆን የተቃወሙት ምዕራባውያን፤ ሩሲያን ያዳክማሉ ያሉዋቸው ማዕቀቦች ሲጥሉ እየተስተዋሉ ነው።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ ባደረገው ስብሰባ ሩሲያ ዩክሬንን መዉረሯን የሚያወግዘዉን የዉሳኔ ሀሳብ በአብላጫ ድምጽ ማጸደቁም እንዲሁ የሚታወስ ነው።