"በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ እየቀረበ እንዳልሆነ የሚናፈሰው ወሬ ሐሰት ነው" ዶ/ር ሙሉ
በክልሉ የመብራት፣ የውሃ እና የባንክ አገልግሎቶች በበርካታ አካባቢዎች መጀመራቸውንም አንስተዋል
አርሶ አደሩ እህል በሚሰበስብበት ወቅት ውጊያ መጀመሩ የሰብዓዊ ቀውስ እንዲባባስ ማድረጉን ዶ/ር ሙሉ ተናግረዋል
"በትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ እየቀረበ እንዳልሆነ የሚናገሩ አካላት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት አስበው ነው" ሲሉ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የፌዴራል መንግሥት በክልሉ የተጠናከረ ሰብአዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
ዶክተር ሙሉ ነጋ እንዳሉት፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ስራውን ሲጀምር ለዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ትኩረት አድርጎ ነው።
ነገር ግን የሰብአዊ ድጋፍ ስርጭቱ በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይደርስ "የጥፋት ቡድኑ" እንቅፋት እንደነበረ አስታውሰዋል።
ሕወሓት የጭነት ተሽከርካሪዎችን አውድሞና የቀሩትን ይዞ መጥፋቱን ጠቅሰዋል።
አርሶ አደሩ እህል በሚያጭድበትና በሚሰበስብበት ወቅት "የጥፋት ቡድኑ" ችግሩን መፍጠሩ ለሰብዓዊ ቀውሱ መባባስ አንድ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ያም ሆኖ አሁን ላይ በትግራይ ክልል 'የሰብዓዊ ድጋፍ እየቀረበ አይደለም' በሚል የሚናፈሰው ወሬ ሐሰት መሆኑን ያነሱት ዶ/ር ሙሉ መረጃውን የሚያናፍሱ አካላት "የፖለቲካ ትርፍ በመፈለግ የሚፈጽሙት ድርጊት" እንደሆነም ጠቁመዋል።
"በጥፋት ቡድኑ ምክንያት ህዝቡ ያለ መብራትና ውሃ በመቆየቱ ለከፍተኛ ችግር ተዳርጓል" ያሉት ዶ/ር ሙሉ፣ የፌዴራል መንግስት ችግሩን ለመፍታት ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
በክልሉ የመብራት፣ የውሃ እና የባንክ አገልግሎቶች በበርካታ አካባቢዎች መጀመራቸውን አንስተው፤ አገልግሎት ባልተጀመረባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ደመወዝ ላልተከፈላቸው የመንግስት ሰራተኞች እንዲከፈላቸው እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የትግራይ ክልልን መልሶ በመገንባት ሂደት ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም ዶክተር ሙሉ ጥሪ አቅርበዋል።