ሱዳናውያንን ወደ ግብጽ ለማሻገር ሾፌሮች 40 ሺህ ዶላር እየጠየቁ ነው ተባለ
በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ጦርነቱን ሽሽት ወደ ጎረቤት ሀገራት እየተሰደዱ ነው
ጦርነቱ በሁሉም ቦታዎች መስፋፋቱን ተከትሎ ከካርቱም ዜጎችን በአየርም ሆነ በየብስ ማስወጣት ቆሟል ተብሏል
በሱዳን ከ15 ቀን በፊት በብሄራዊ ጦሩ እና በፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ መካከል የተጀመረው ጦርነት አሁንም ሊበርድ አልቻለም፡፡
በዚህ ጦርነት ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ዜጎች ቁጥር ከ450 በላይ የደረሰ ሲሆን ከ10 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መኖሪያ የነበረችው ካርቱም ዋነኛ የጦርነት ቀጠና ሆናለች።
በርካታ የዓለማችን ሀገራትም ዜጎቻቸውን ከካርቱም ያስወጡ ሲሆን ጦርነቱ በካርቱም እና ሌሎች ከተሞችም መስፋፋቱን ተከትሎ አሁን ላይ ዜጎች መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከሱዳን ወደ ጎረቤት ግብጽ በአውቶቡስ ለማስወጣት ሾፌሮች እስከ 40 ሺህ ዶላር እየጠየቁ ነው ተብሏል።
ከዚህ በፊት ተመሳሳይ አገልግሎት ለማግኘት ይጠየቅ የነበረው 3 ሺህ ዶላር ብቻ እንደነበር ነው የተጠቀሰው።
የተለየ የመግቢያ ፈቃድ ያላቸው አውቶብሶች ሾፌሮች ናቸው 40 ሺህ የአሜሪካ ዶላር እየጠየቁ የሚገኙት።
ፈቃድ ካላቸው አውቶብሶች ውጭ ወደ ግብጽ መግባት አይቻልም የተባለ ሲሆን፥ ይህን ተከትሎም በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን በድንበር ላይ እንደሚገኙ ተዘግቧል።
በካርቱም እና በሌሎች ከተሞች ጦርነቱ እየተባባአሰ መቀጠሉንን ተከትሎም ጦርነቱ እንዲቆም አልያም የተኩስ አቁም ግፊት እንዲደረግ ነዋሪዎች በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡
የሱዳን ተፋላሚ ሀይሎች የተኩስ አቁም ለማድረግ ቢስማሙም ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ እንደማይተገበር በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል መሪ የሆኑት ጀነራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ የአየር ላይ ድብደባ ካልቆመ ለድርድር እንደማይቀመጡ ተናግረዋል፡፡
ተመድ፣ ኢጋድ እና ሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራት የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች ለድርድር እንዲቀመጡ ጫና በመፍጠር ላይ ሲሆኑ በቀጣይ ድርድር ሊጀመር እንደሚችል ይጠበቃል፡፡