ምርጫው ባለፈው ዓመት መካሄድ ይገባው የነበረ ሲሆን በተለያዩ ምክንያቶች ተራዝሞ የቆየ ነው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ከተመረጡ በኋላ ነገ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገሪቱ ምርጫ ይደረጋል፡፡
የነገው ምርጫ፤ የቀድሞው ገዥ ፓርቲ ኢህአዴግ በ2007 ዓ.ም ተካሂዶ የነበረውን ምርጫ 100 በ 100 ማሸነፉን ከገለጸ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረግ ነው፡፡
ምንም እንኳን ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም ተካሂዶ የነበረውን ምርጫ ኢህአዴግ ሙሉ በሙሉ ማሸነፉን መግለጹ የሚታወስ ቢሆንም፤ የምርጫው ውጤት ተነግሮ አዲስ መንግስት ከተቋቋመ ከወራት በኋላ በኢትዮጵያ ጸረ መንግስት ተቃውሞዎች ነበሩ፡፡
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም በምርጫው አሸንፈው ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆኑም ፓርቲያቸው ኢህአዴግ ለማካሄድ አቅዶት ለነበረው “የማሻሻያ ስራዎች የመፍትሔ አካል ለመሆን” በሚል በራሳቸው ፈቃድ ሥልጣን መልቀቃቸው ይታወሳል፡፡
የ2007 ዓ.ም ምርጫ ውጤት ከተነገረ በኋላ በተካሄዱ ተቃውሞዎች ኢህአዴግ ሊቀመንበር ለመቀየር በመገደዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ አቶ ኃይለማሪያምን በመተካት የገዥው ፓርቲና የመንግስት መሪ ሆነዋል፡፡
ምንም እንኳን የሥልጣን ሽግግሩ ሰላማዊ ቢሆንም ተሿሚው ጠቅላይ ሚኒስትር በይፋ በህዝብ የተመረጡ አልነበሩም፡፡
የነገው ምርጫም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይንም ሆነ የፓርቲያቸውን ተመራጭነትና ህጋዊነት ሊረጋገጥ የሚችልበት ነው፡፡
ሀገር አቀፍ ምርጫው ከአንድ ዓመት በፊት ነበር ሊደረግ ታስቦ ነበረው፡፡ ሆኖም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሳይካሄድ ቀርቶ ተራዝሟል፡፡
አሁን ግን ነገ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ/ም ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮችና የፌዴሬሽኑ አባል የሆኑ ክልሎች ይመርጣሉ፡፡
በትግራይ ክልል ባለው አሁናዊ የጸጥታ ችግር ምክንያት ምርጫው የማይካሄድ ከመሆኑም በላይ መቼ እንደሚካሄድ የተባለ ነገር የለም፡፡
ከትግራይ ክልል ውጭም በተለያዩ ምክንያቶች ምርጫ የማይደረግባቸው ቦታዎች ጳጉሜ አንድ ቀን 2013 ድምጽ የሚሰጥባቸው ይሆናል፡፡