በሁሉን አካታች ውይይቱ የህገ መንግስት ማሻሻያን ጨምሮ በርካታ ጉዳዮች ለውይይት ክፍት ይደረጋሉ- አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን
የተመድ የሰብአዊ መብት ምክር ቤት ውሳኔ በኢትዮጵያ ምድር ተፈፃሚ አይሆንም ብለዋል
መንግሰት ትግራይን ጨምሮ በማንኛውም ሀገሪቱ አካባቢዎች ሰራዊቱን የማስፈር መብት እንዳለው ገልጸዋል
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የአፍሪካ፣ የአውሮፓ፣ አሜሪካ፣ ኤስያ እና መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ከአምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ዙሪያ ማብራሪያ ተሰጥተዋል።
አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በማብራሪያቸው፣ የፖለቲካ ፍላጎትን መሠረት አድርጎ በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ ኢትዮጵያ እንደማትቀበል ተናግረዋል።
የፖለቲካ ፍላጎት ባላቸው አካላት ገፋፊነት እና አስተባባሪነት የተላለፈው ውሳኔ በኢትዮጵያ ምድር ተፈፃሚ እንደማይሆን መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያን አግባብነት ካላቸው ተቋማት ጋር ትብብር ስታደርግ መቆየቷን አንስተዋል። የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመመርመር ተግባራዊ ማስተካከያዎችን ለመውሰድ የሚያስችል ተቋማዊ አቅም እንዳላትም ጠቅሰዋል።
ቀደም ሲል የተመድ የሰብዓዊ መብት ተቋም እና የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባደረጉት የጋራ ምርመራ የተሰጡትን ምክረ ሀሳቦችን ለመተግበር ኢትየጵያ ተግባራዊ አንቅስቃሴ በማድረግ ላይ በምትገኝበት ጊዜ የተላለፈ ውሳኔ መሆኑንም ገልጸዋል።
ም/ቤቱ ህወሓት በወረራ በቆየባቸው የአማራ እና አፋር አካባቢዎች የፈጸማቸውን መጠነ ሰፊ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጥፋት በማውገዝ ምርመራ እንዲካሄድ ውሳኔ ቢያሰተላልፍ ኖሮ ተገቢና የሚያስመሰግነው እንደነበርም ገልጸዋል።
የህወሃት ቡድን የእርዳታ አቅርቦት ለማስተጓጎል የሚወስደው የእብሪት ተግባርን የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በቸልታ መመልከቱን ጠቅሰው፤ በመንግስት በኩል ግን የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚቻለውን ሁሉ ማድረጉን አመልክተዋል።
አምባሳደር ሬድዋን በማብራሪያቸው አክለውም የህወሓት ሀይል በደረሰበት ምት ይዟቸው የነበሩ አብዛኛው የአፋር እና የአማራ አካባቢዎችን በማስለቀቅ በመንግሥት የፀጥታ ሀይሎች ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ ገልፀዋል።
ይህም ቡድኑ ለሰላም ሲል በወረራ ከያዝኳቸው አካባቢዎች ለቅቂያለሁ ማለቱ ከተጨባጩ እውነታ ጋር የሚቃረን ስለመሆኑም አንስተዋል።
መንግስት ቡድኑ በሚሸሽባቸው እያንዳንዱ የትግራይ መንደሮች እግር በእግር በመከተታል የመግባት ፍላጎት የሌለው መሆኑን ያነሱት ሚኒስትር ደኤታው፣ ነገር ግን ቡድኑ መቸውም ቢሆን መልሶ ጥቃት የማድረስ አቅሙ የተዳከመ መሆኑ ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
አክለውም የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትን ማስጠበቅ የመንግስት ኃላፊነት እንደመሆኑ መጠን፣ ትግራይን ጨምሮ በማንኛውም ሀገሪቱ አካባቢዎች ሰራዊቱን የማስፈር መብት እንዳለው አመላክተዋል።
በቀጣይም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ያለመ ሁሉን አካታች ዉይይት እንደሚካሄድ ጠቅሰው፣ የህገ መንግስት ማሻሻያን ጨምሮ በሀገሪቱ ስምምነት ያልተደረሰባቸው ጉዳዮችን የተመለከቱ ጉዳዮች ለውይይት ክፍት እንደሚደረጉ ገልጸዋል።