ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ከሲሲ የተላኩ መልዕክቶችን ይዘው እስካሁን ወደ ተለያዩ 6 ሃገራት ተጉዘዋል
ግብጽ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሃገራትን እያግባባች ነው
የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ከፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ የተላኩ መልዕክቶችን በመያዝ ወደተለያዩ ሃገራት እየሄዱ መሆናቸው ተገለጸ፡፡ የሚኒስትሩ ጉዞና የፕሬዝዳንቱ መልዕክትም ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባቸው ባለችው ግድብ ላይ ያተኮረ ነው፡፡
ሽኩሪ በኩዌት፣ሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣ ኢራቅ፣ኦማን፣ዮርዳኖስና ባህሬን በመሄድ ስለግድቡ የማግባባት ስራ እየሰሩ ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡
የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አህመድ ሃፊዝም ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡
ለጉብኝት በሄዱባቸው ሃገራት ሁሉ የድርድሩን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ መልዕክቶችን እንደሚያደርሱም ነው የተናገሩት፡፡
ትናንት እሁድ ግድቡን በተመለከተ ከአል ሲሲ የተላከ መልዕክትን ለኩዌቱ ኢሚር አድርሰዋል፡፡
የኦማንና የኩዌት መሪዎች ከግብጽ ጎን እንቆማለን ስለማለታቸውንም ከግብጽ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከሰሞኑ ኢትዮጵያና ግብጽ በግድቡ ዙሪያ እሰጣገባ ውስጥ ገብተዋል፡፡
ግብጽ በአሜሪካ የተዘጋጀውን ሰነድ ፈርማለች፡፡
ሰነዱን በወጉ ማጤንና ለመፈረም የጀመረችውን መመካከር ማጠናቀቅ እንዳለባት ለዚህም ጊዜ እንደምትፈልግ ያስታወቀችው ኢትዮጵያ ግን አልፈረመችም፡፡
የታዛቢነት ሚና የነበራት አሜሪካ ሰነድ አዘጋጅ ሆና መቅረቧንም ተችታለች፡፡
ግድቡን የመገንባት፣ ውሃ ሙሌቱንም የማከናወን ስራውን እንደምትቀጥል ማስታወቋም የሚታወስ ነው፡፡
በአንጻሩ ጥቅሜ ይነካል ያለችው ግብጽ ለአረብ ሊግ አባል ሃገራት ያቀረበችው የድጋፍ ሃሳብ በሊጉ አባል ሃገራት ቢጸድቅም ሱዳን መቃወሟ አይዘነጋም፡፡