“ግብጽ የአባይን ውኃ በረሃዎቿን ለማልማት በመቶ ኪሎ ሜትሮች ርቀት እየጠለፈች ነው”-አቶ ገዱ
“ግብጽ በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ ስትገነባ አማክራን አታውቅም”
በህዳሴ ግድቡ ድርድር ዙሪያ ኢትዮጵያ የምታዘጋጀው ሰነድ ምን የተለየ ነገር ይዟል?
በህዳሴ ግድቡ ድርድር ዙሪያ ኢትዮጵያ የምታዘጋጀው ሰነድ ምን የተለየ ነገር ይዟል?
ከሚያዚያ 2011 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን እያገለገሉ ያሉት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ፣ግብጽና ሱዳን መካከል ሲካሄድ የቆየውን የሚኒስትሮች ስብሰባ እየመሩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ አቶ ገዱ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ባለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ የድርድር ሂደትና ቀጣይ ዕቅድ ዙሪያ እንዲሁም በኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት ዙሪያ ከአል ዐይን ኒውስ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡
ከሚኒስትሩ ጋር የተደረገውን ሙሉ ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
አል- ዐይን፡- ኢትዮጵያ በሃገር ቤት የምሰራቸው ስራዎች አልተጠናቀቁም፤ በመሆኑም በውይይቱ ላይ አልገኝም ብላ ከመጨረሻው ውይይት ቀርታለች፡፡ በቀጣይ ምን ለማድረግ አስባለች?
አቶ ገዱ፡- ኢትዮጵያ በዚህ በባለፈው ሲካሄድ በነበረው ድርድር ላይ ድርድሩ አያስፈልግም የሚል አቋም የላትም፡፡ በዓባይ ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ እየገነባቸው ባለው የዓባይ ግድብ ላይ የተጀመረው ድርድር በአግባቡ ሁሉንም ሃገሮች ተጠቃሚ በሚያደርግ መንገድ መቋጨት አለበት የሚል እምነት አለን፡፡ድርድር እያካሄዱ ያሉት ሶስት ሃገሮች ኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብጽ ናቸው፡፡ አትዮጵያ የግድቡ ባለቤት ነች፡፡ ይህንን ግድብ የምትገነባው እስካሁን ድረስ የኃይል አቅርቦት የማያገኙትን ከ 65 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን የመብራት ተጠቃሚ እንዲሆኑና እንደዚሁም ደግሞ ኢትዮጵያ አሁን ለልማቷ የሚያስፈልጋትን ኃይል ለማመንጨት ያለመ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ውሀ ልታገኝ የሚገባትን ለመጠቀም ነው እየሰራች ያለችው ይህን ግድብ፡፡ በአንጻሩ ኢትዮጵያ ይህንን ግድብ በምትሰራበት ጊዜ ለታችኞቹ የተፋሰሱ ሃገራት ከፍተኛ ጥቅም ይዞ የሚመጣ ግድብ ነው፡፡ እነርሱም ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡በሌላ በኩል ደግሞ ጥያቄ አላቸው፡፡ ማለትም በውሀው ላይ ህልውናቸው የተመሰረተ የታችኞቹ ሀገሮች ይህ ግድብ በሚሰራበት ጊዜ የጎላ ተጽዕኖ እንዳይደርስባቸው አስፈላጊው ጥንቃቄ የተደረገ ቢሆንም ሙሉ መተማመን እንዲፈጠር መነጋገሩ፣ በግልጽነት መደራደሩ እና የሚያነሱትን ኮንሰርን (ሀሳብ) በማየት ተጠቃሚ መሆን በሚያስችል ደረጃ ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋል ብለን እናምናለን፡፡ ስለዚህ ድርድሩ ጭራሽ መቋረጥ አለበት የሚል እምነት የለንም፡፡ ለማንም መቋረጡ አይጠቅምም ተነጋግሮ ሁሉንም ሀገሮች ኢትዮጵያን፣ ግብጽን፣ ሱዳንን ተጠቃሚ በሚያደርግበት መንገድ ፍትሐዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ይህንን ውሀ እንድንጠቀምበት በሚያስችል አግባብ ስምምነት መደረስ አለበት፤ ለዚህም ደግሞ ድርድሩ መቀጠል መቻል አለበት ብለን እናምናለን፡፡ ባለፈው በተወሰነ ደረጃ የተቃወምነው ድርድሩን አይደለም፡፡ ድርድሩማ የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ ተደራድሮ ስምምነት ላይ መድረስም የግድ ይለናል፡፡የተቃወምነው አካሄዱ ላይ ነው፡፡ አካሄዱ ላይ ስል ምን ማለት ነው ገና ያላለቁ ጉዳዮች አሉ፡፡ሶስቱ ሀገሮች ተስማምተን ያልጨረስናቸው ነገሮች አሉ፡፡እነዛ ሳያልቁ ወደፊርማ እንሂድ መባሉ አግባብነት የለውም ብለን እናምናለን፡፡ እንደገና ደግሞ ነገሮቹን እኛ ሶስቱ ሃገሮች ተደራድረን ባለቤቶቹ ስምምነት ላይ መድረስ እየቻልን በታዛቢነት የነበሩት አካላት ከታዛቢነት ወጣ ያለ አዝማሚያ በማሳየታቸው ይህ መስተካከል አለበት የሚል ነው አቋም የያዝነው እንጂ ድርድሩ ይቋረጥ የሚል እምነት የለንም፡፡ ወደፊትም ድርድሩ ይቀጥላል ብለን ነው የምናምነው፡፡
አል- ዐይን ፡- በተጨማሪም የግድቡ ደህንነት፣ኢትዮጵያ ውሀ ለማጠራቀምና ለመሸጥ ነው ዓላማዋ እያለች ግብጽ ቅሬታ ታቀርባለች፤ ኢትዮጵያስ ምን ትላለች?
አቶ ገዱ፡- አሁን እንግዲህ ምንድነው በግብጾች በኩል የሚነሱ የተለያዩ ሃሳች አሉ፡፡ለምን እንደሚጠቅማቸው አይገባኝም በኔ በኩል፡፡ ኢትዮጵያ ያላሰበችውን እንድታስብ ለምን እንደሚያደርጉ፤ የመጀመሪያው ጉዳይ ሙሌቱን በተመለከተ ግድቡ በሚሞላበት ጊዜ ከሶስት እስከ አራት ዓመት ባለው ሙሉ በሙሉ መሙላት ይቻላል፡፡ይህንን ግብጾችም ያውቁታል፡፡ ነገር ግን ቶሎ በሚሞላበት ጊዜ በታችኞቹ ላይ የጎላ ተጽዕኖ እንዳያደርስ አንዳንድ ጥያቄዎች ስለተነሱ እሺ እስከ ሰባት ዓመት ድረስ መሄድ ይችላል፡፡ምክንያቱም ከተሞላ በኋላ በሁለተኛው በሶስተኛው ዓመት ኃይል እያመነጨ የሚቀጥል ስለሆነ ወደ ከፍተኛ የማመንጨት ደረጃው እስከሚደርስ ድረስ ቀስ በቀስ የመሙላቱ ስራ እስከ ሰባት ዓመት ድረስ ሊሆን ይችላል፤ በተለይም ደግሞ በወቅቱ ከሚኖረው ዝናብ ጋር፣ የውሀ መጠን ጋር ተያይዞ መታየት ያለባቸው ነገሮች አሉ ብለን የታችኞቹን ሃገሮች በጎላ ሁኔታ ተጽዕኖ እንዳያደርስባቸው በጣም ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ነው ማኔጅ ለመድረግ እየተሰራ ያለው፡፡ ስለዚህ አንዱ የበለጠ ግልጽ ለማድረግ እየሰራን ያለነው ይሄ ነው፡፡ የት ላይ ነው ግድቡ ውሀ ሲሞላ ጉዳት የሚያደርስባቸው? ተመካክረን፣ተነጋግረን በአብዛኞቹ ጉዳዮች እኮ እየተቀራረብን ነው የመጣነው፡፡ አሞላሉን በተመለከት ምንድነው የተባለው፣ ድርቅ የሚያጋጥም ከሆነ በተለይም የተራዘመ ድርቅ የሚያጋጥም ከሆነ ውሀ አሞላሉ ላይም በዚያው መጠን የሚዘው የውሀ መጠን እንዲቀንስ፣ ቀስበቀስ እንደዲያዝ ተብሎ እኮ ቢያንስ በውይይት ደረጃ መግባባት የተደረሰባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ግትር ናት? በሶስት ዓመት መሙላት የምትችለውን ግድብ የታችኞቹ ሀገራት የሚያነሱትን ስጋት ለመቀነስ እስከ ሰባት ዓመት ማራዘም ግትርነቴን የሚያመለክት ነው? ሁለተኛ ግድቡን በተመለከተ የግድቡ ደህንነት ያሰጋናል የሚሉት ከመጀመሪያው ግድቡ እንደተጀመረ እኮ በዓለም ደረጃ አሉ የሚባሉ ከአውሮፓ ከፈረንሳይ፣ ከእንግሊዝ፣ ከግብጽ፣ ከሱዳን፣ ከኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ በመስኩ አንቱ የተባሉ ባለሙያዎች እንዲገመግሙት ተደርጎ ዓለም አቀፍ ስታንዳርዱን (ደረጃውን) ያሟላ ነው ተብሎ ኦልሬዲ መግባባት ላይ የተደረሰበት እኮ፡፡ አሁን እንደገና የግድቡ ደህንነት ያሰጋናል የሚለውን ለምን ያመጡታል? እሱን ሙያተኞች በተሳተፉበት ሁሉም ሰነድ እኮ ተሰጥቷቸው ገምግመውታል፡፡ እዩት፤ ችግር ካለ እናስተካክለዋልን፤ ተብለዋል እኮ፡፡ አይተውታልም፤ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድም ገምግመውታል፡፡ ሳይንሳዊ የሆነ ግምገማ የሚያካሂዱ፣ በመስኩ አሉ የተባሉ ባለሙያዎች ረዘም ያለ ጊዜ ወስደው ተወያይተውበት ገምግመውት ኢትዮጵያ ከዲዛይን ጀምሮ ግንባታው እየተካሄደበት ያለው አግባብ ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ በሚያሟላ መንገድ ነው ብለው ምስክርነት የሰጡበትና የተስማማንበት ጉዳይ ነው፡፡ እና እነዚህን እዩና እናንተን የሚያሰጋችሁ ነገር ካለ እኛ እናስተካክለዋለን ተብሎ ክፍት የተደረገውና ሰፊ ውይይትና ድርድር እያካሄድን ያለነው እኮ ግትርነትን የሚያመለክት አይደለም፤ እንዲያውም እነሱ ትልልቅ ግድቦች ሲገድቡ እኛን አማክረውን አያውቁም፡፡
እኛ እኮ በኛ ግድብ ላይ ነው፤ ከራሳችን ሀገር ከሚመነጭ ውሀ፣ ከራሳችን የግዛት ክልል ውስጥ፣ በራሳችን ህዝብ መዋጮና መንግስት የሚሰራ ግድብ፣ በሶስቱም ሀገራት መተማመንና ግንኙነት እንዲዳብር በማሰብ እኮ ነው ኢትዮጵያ ሁሉንም ነገር ግልጽ አድርጋ እየሞከረች ያለችው፡፡
ጥያቄ፡ አል- ዐይን ፡- ግብጽ ኢትዮጵያ ግድቡን ስትገነባ አርሶ አደሮቼ፣ በዓሳ እርባታ የሚተዳደሩ ዜጎቼ ይጎዳሉ ትላለች፡፡ ይህን እንዴት መለሳችሁት?
አቶ ገዱ፡- እንግዲህ ይሄ ግድብ የሚይዘው የውሀ መጠን በአግባቡ በጥናት ላይ ተመስርቶ፣ ታችኞቹ ሀገራት ላይ ቅድም እንደገለጽኩት የጎላ ተጽእኖ በማያደርስበት ሁኔታ፣ አባይ በዓመት የሚፈሰው እኮ አማካኝ ፍሰቱ 49 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ነው፤ በዓመቱ የሚፈሰው፡፡ እሺ ኢትዮጵያስ አንድ ዓመት ትያዘው! በሚቀጥለው ዓመት እኮ ፈሶ ይሄድ እንደሆነ ነው እንጂ እንዴት አድርጎ ማስቀረት ይቻላል ይሄን ትልቅ ውሃ፡፡ የኢትዮጵያ ዓላማ ደግሞ ግድቡን እኮ ውሀ እንዲዝ አይደለም ዓላማው፤ ሀይል ማመንጨት ነው አላማው፤ አንድ ጊዜ ውሀ ከሞላ በኋላ ማለት ሀምሌ ነሀሴና በተወሰነ ደረጃ መስከረም ላይ ከፍተኛ የውሃ ፍሰት ባለበት ጊዜ ውሃ ይያዛል፡፡ በሌሎች ወራቶች፣ ጥቅምት ህዳር ደግሞ እስከ ሰኔ ድረስ ባለው መልሶ ይለቀቃል ማለት ነው፡፡ ይሄ ውሃ እኮ ተይዞ የሚቀር አይደለም፡፡ ከፍተኛ የውሀ ፍሰት ባለበት ጊዜ ውሀ ይያዝና ዉሀው ደግሞ በበጋ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ ወንዝ ውስጥ ስለሚቆይ በዛ ወቅት ከፍተኛ የሆነ ኃይል አመንጭቶ ውሃው ወደ ታች ይፈሳል፡፡ አንዴ ከተሞላ በኋላ የኢትዮጵያ ዓላማ ውሀ መልቀቅ ነው እንጂ ውሀ መያዝ አይደለም፡፡ ውሀ ለምንድነው ኢትዮጵያ የምትይዘው? ግድቡ ኃይል ሲያመነጭ ውሀ አይወስድም፤ እንዴት ብሎ ነው አሳ አጥማጆቹ፤ በመስኖ ስራ የሚተዳደሩት ገበሬዎች ይጎዳሉ ብለው ሚያራምዱት ፕሮፓጋንዳ በፍጹም አስኬድም፡፡ እንነጋገር ከተባለ እኮ በአዲስ መልክ ገና በረሃ እያስገቡት ነው ከተፈጥሯዊው መፍሰሻ አካባቢው አውጥተው ሌላ ሩቅ ቦታ በብዙ መቶ ኪሎ ሜትሮች የሚቆጠር ቦታ ወስደው በረሃ እያለሙበት ነው ያለው፡፡ ይሄ ልማት ነው ይቀጥሉ፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ የድርሻዋን መጠቀም አለባት፤ ሱዳን የድርሻዋን መጠቀም አለባት፡፡ ለዓረቡ አለምም ኢትዮጵያ ውሀውን ዝግት አድርጋ ልታስቀርብን ነው የሚለው የተሳሳተ መረጃ ነው፤ እንደገለጽኩት ኢትዮጵያ ውሀ ይዞ ከማከማቸት ምን ትጠቀማለች? መስኖ አናለማበት ግድቡ እየተሰራ ያለው ከኢትዮጵያ የድንበር ክልል ወደ ሱዳን ተጠግቶ 20 ምናምን ኬሎሜትር ርቀት ላይ ነው፡፡ አንድ ጊዜ ሀይል አመንጭቶ ከወጣ በኋላ ወደ ሱዳንና ግብጽ ነው የሚፈሰው፡፡ ውሀ መያዝ አይደለም ዓላማችን፤ ኃይል ማመንጨት ነው ዋናው ዓላማችን፡፡ ኃይል ከመነጨ በኋላ ውሀው ይሄዳል፡፡ ትልቁ ችግር የሚመስለኝ ኢትዮጵያ የዉሀው ባለቤት፣ ውሀው የሚመነጭባት ሀገር ሆና እያለች ከዚህ ወንዝ መጠቀም ያለባትን የራሷን ድርሻ ተፈጥሮ የሰጣትን ጸጋ ለመጠቀም የምታደርገውን ጥረት ለመገደብና እነሱ እየተጠቀሙ የኢትዮጵያ ህዝብ በጨለማ እንዲኖር ከመፈለግ የሚመነጭ ካልሆነ በስተቀር የኢትዮጵያ መንግሰት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ግብፅም ሆነ ሱዳን እንዲጎዱ አንድም ቀን አስበው አያውቁም፡፡ ምክንያቱም አኛ የተሻለ ኑሮ እንድንኖር ነው እንጂ ሌሎች እንዲጎዱ አይደለም ፍላጎታችን፡፡ እና ያልሆነ ነገር ለምን ያስባሉ? የማይገባኝ ነገር ኢትዮጵያ ያላሰበችውን “ኔጌቲቭ” (አሉታዊ) ነገር፣ በታችኞቹ ሀገራት ላይ እንዲደርስ የማትፈልገውን ነገር ኢትዮጵያ እንዳሰበች አድርጎ ማስወራት፣ ቅስቀሳ ማካሄድ፣ ሰፊ ዘመቻ ማካሄድ ማንንም አይጠቅምም፡፡ ለተመልካቹ ለዓረቡ አለምም አይጠቅምም፡፡ የተሳሳተና የሀሰት መረጃ የሚያስተላልፍ ነው፡፡ በሀሰት መረጃ ደግሞ ነገ እውነቱ ሲታይ ይገለጣል፡፡ የዓረብ ሚዲያዎች አንደናንተ እስኪ እየመጡ ይዩት፡፡ የዓረቡ ዓለም መንግስታትም ልዑካኖቻቸውን ይላኩ፡፡ ይዩት፤ አሁን ይዩት፤ ውሀ መሙላት ሲጀምርም ይዩት፡፡….
አል-ዐይን፡- ኢትዮጵያ በግድቡ ዙሪያ አዲስ ሰነድ እያዘጋጀች ነው እየተባለ ነው፡፡ ይህ እየተዘጋጀ ነው የተባለው ሰነድ ይዘት ምንድነው?
አቶ ገዱ፡- እንግዲህ ምንድነው በዛ ድርድር ወቅት ከይዘት አኳያ የቀረቡ ሃሳቦች አሉ፤ እኛ የማንቀበላቸው፡፡ የግድቡን አሞላል ጊዜ የሚያስረዝሙ ከመጠን በላይ ሲጓተት ኢትዮጵያ ከግድቡ ልታገኝ የምትችለውን ኃይል በአግባብ እንዳታገኝ የሚያደርግ፣ እንደገና ደግሞ ወደላይኛው በቀጣይ በተፋሰሱ ለሚካሄዱ ልማቶች እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ የስምምነት ሃሳቦች፣ ከዛም በድምሩ ስንመለከተው ደግሞ ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ ይህንን ግድብ የምትሰራው በጣም ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ አውጥታ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ወደ አምስት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ አውጥተው ነው እየሰሩት ያለው፡፡ ይህንን ያህል ገንዘብ የወጣበት ግድብ በሙሉ ኃይሉ ኃይል ማመንጨት አለበት፡፡ አሁን በድርድር የቀረቡት የተወሰኑት ሃሳቦች ግድቡ በሙሉ አቅሙ ሃይል እንዳያመነጭ የሚያደርጉ ስለሆነ ይህን ያህል ገንዘብ-በሌለ ገንዘብ፣ በሌለ አቅማችን አውጥተን የሰራነው ግድብ የሚያመነጨው ኃይል ዝቅተኛ እንዲሆን ማድረግ አግባብነት የለውም ብለን እናምናለን፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ዓባይ ከኢትዮጵያ የሚመነጭ ቢሆንም የኢትዮጵያ፣የሱዳን፣ የግብጽም የጋራ ሀብት ነው፡፡ በዚህ ወንዝ ላይ ተስማምተን ሁላችንም ወደፊትም ቢሆን ፍትሓዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መጠቀም ይኖርብናል እንጂ ታችኞቹ ሀገሮች እንዳይጎዱ ተብሎ ከወደላይ በኩል ልማት የሚያስቆም አይነት አዝማሚያ መያዝ ተገቢነት የለውም ብለን እናምናለን፡፡ ነገር ግን በእኛ እምነት በአግባቡ ከተጠቀምንበት፣ አንዱ ሌላውን እንዳይጠቀም እንቅፋት በማይሆንበት ሁኔታ በአግባቡ ከተጠቀምንበት፣ የዓባይ ውሀ ለኢትዮጵያም፣ ለሱዳንም፣ ለግብጽም ይበቃል የሚል እምነት ነው ያለን፡፡ እኛ አሁን ከግድቡ ጋር የተያያዘውን ብናነሳ ይህ ግድብ ውሀ ይይዛል፤ ውሀ በሚይዝበት ጊዜ በመጀመሪያው ውሀ ሙሌቱ በሚካሄድበት ጊዜ፣ በአንድ ጊዜ በፍጥነት በሁለት በሦስት ዓመታት ውስጥ መሙላት ይቻላል ግድቡን፡፡ በሁለት በሦስት ዓመታት መሙላት የሚቻል ግድብ ቢሆንም እንኳን በፍጥነት በሚሞላበት ጊዜ ለታችኞቹ ሃገሮች የሚሄደው ውሀ በብዛት ቀርቶ ታችኞቹ ሀገሮች እንዳይጎዱ በማሰብ ኢትዮጵያ የሙሌት ጊዜውን በሁለት በሦስት ዓመታት መጨረስ የምትችለውን እስከ ሰባት ዓመት ድረስ ማራዘም የምትችል መሆኑን በግልጽ አስቀምጣለች፡፡ ምን ማለት ነው ታችኞቹ ሀገሮች ሱዳንና ግብጽ በምንም ተአምር የጎላ ጉዳት እንዲደርስባቸው ኢትዮጵያ አትፈልግም፡፡ ምን እናገኛለን ከነሱ መጎዳት? የነሱ መጎዳት እኮ ምንም ጥቅም አይሰጣትም ለኢትዮጵያ፤ እኛም እንጠቀም እነሱም ይጠቀሙ ነው የእኛ አቋም፤ እየተሰራ ያለውም በዚህ አቅጣጫ ነው፡፡ እኛ እየተዘጋጀ ያለው ሰነድ ከዚህ በፊት የነበረንን አቋም ምናልባት ለተደራዳሪ ወገኖች በተለይም ለግብጾቹ ግልጽ ያልሆኑ ነገሮች ካሉ መተማመን ላይ በሚያደርስ መንገድ የበለጠ ግልጽ የማድረግ እና የማጠናከር ስራ ለመስራት ነው፡፡ እና ግድቡን የጎላ ተጽዕኖ በማያሳርፍበት መንገድ እንዴት አድርገን እንሞላዋለን? እንዴት አድርገን እናስተዳድራለን? ለሌሎችም ግልጽ በሚሆን መንገድ በሌላ በኩል ደግሞ ለኢትዮጵያ ህዝብ ግልጽ በሚሆን መንገድ የበለጠ አቋሙን የማጠናከር፣ እንደገና ደግሞ የሚመለከታቸው አካላት እንዲወያዩበት፣ እንዲመክሩበት የያዝነው አቋም የት ላይ ድክመት አለበት? የት ላይ ጥንካሬ አለው? ብሎ የጋራ የህዝብ ፕሮጀክት እንደመሆኑ መጠን የሚመለከታቸው ሙያው፣ ችሎታው ያላቸው ሰዎች በሰፊው እንዲመክሩበት ከዛም ደግሞ የደረስንበትን አቋም ለህዝብ እንዲደርስ ለማድረግ ታስቦ ነው እያዘጋጀን ያለነው፤ እንጂ አዲስ መደራደሪያ ሃሳብ ልናመጣ አይደለም፡፡ የነበረውን የበለጠ ግልጽ ማድረግና የማጠናከር ስራ ነው እየሰራን ያለነው፡፡
አል- ዐይን፡- የአፍሪካ ህብረት በዚህ ድርድር ላይ ቢሳተፍ ኢትዮጵያ ምን ምላሽ ይኖራታል?
አቶ ገዱ፡- ከሁሉም በፊት በግድቡ የድርድር ጉዳይ ላይ መሰረታዊ ጉዳዮች ምንድን ናቸው- ግድቡ እንዴት ውሀ ይሞላ? ዉሀ ከተሞላ በኋላ እንዴት ውሀው ይለቀቅ? እና በታችኞቹ የተፋሰስ ሃገራት የጎላ ተጽዕኖ በማያደርስ መንገድ የሚተዳደርበትን ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡ እነዚህ ናቸው የድርድር ነጥቦች ፡፡ እነዚህ ደግሞ የቴክኒክ ሙያተኞች ጉዳዮች ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህን የቴክኒክ ጉዳዮች በጋራ ሶስቱ ሃገሮች ሦስታችን ራሳችን ተነጋግረን ልንፈታቸው የምንችላቸው ናቸው የሚል ነው የኢትዮጵያ መሰረታዊ ፍላጎት፡፡ የበለጠ በጉዳዮቹ ላይ በእውነቱ ለመናገር ለመግባባት ሌላ ሦስተኛ ወገን ከሚያወያይ፣ከሚያደራድር ይልቅ እኛው ራሳችን ብንደራደር፣ብንነጋገር መግባባት እንችላለን የሚል ዕምነት አለን፡፡ ይህ በመሆኑ ምክንያት በጣም ትኩረት ሰጥተን የቆየነው የሦስቱ ሃገሮች የእርስ በእርስ ድርድር እንዲያካሂዱና በዛ ላይ መቋጫ እንዲሰጡት እና ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ማድረግ ላይ ነው፡፡ ነገር ግን በግብጾች በኩል የተለያዩ አካላት እንዲገቡ ፍላጎት አለ፡፡ አሜሪካኖች እንዲያግዙም ዋናው ጥሪ የቀረበው ከግብጽ በኩል ነው፡፡ ወደፊት አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የአፍሪካ ህብረት ቢገባ ለእኛ የጋራ ድርጅታችን ነው ብለን እናምናለን፡፡ አፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያም፣ የሱዳንም፣ የግብጽም ነው፡፡ እንደገና ደግሞ በአፍሪካ አሁን በቅርብ ጊዜ ችግርን በማቃለል ረገድ የተሻለ ውጤትም እየታየ ነው፡፡ የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካውያን በራሳቸው መፍታት የአፍሪካን ባህል መሰረት አድርጎ፣ የአፍሪካን ዕውቀት ተጠቅሞ ችግሮችን የመፍታት ሁኔታ የተሻለ ውጤት እያመጣ ነው እየተመለከትን ያለነው፡፡ ስለዚህ የአፍሪካ ህብረት በዚህ ጉዳይ ላይ ቢገባ እኛ ችግር አለው ብለን አንወስድም፡፡ የበለጠ እንዱያውም ሊያግዝ ይችላል ብለን እናምናለን፡፡ ነገር ግን እዛ ሁሉ ከመሄድ ራሳችን ሦስታችን ሃገሮች ተነጋግረን ብንፈታ የተሻለ ነው፡፡ ከሁሉም የቀለለው መንገድ ያ ነው ብለን ነው የምናምነው፡፡
አል- ዐይን፡- ለግብጽ ህዝብና ለቀሪው ዓለም ምን ይላሉ?
አቶ ገዱ፡- ለዓረብ ዓለምም ሆነ ለመላው የዓለም ህዝብ እንዲሁም ለግብጽ ህዝብ፣ ለሱዳን ህዝብ ማስተላለፍ የምፈልገው ይህ ግድብ በምንም ተአምር የግጭት ምንጭ ሊሆን አይችልም፤ ይህ ግድብ ኃይል ያመነጫል፤ ይህ ኃይል ለኢትዮጵያና ለጎረቤቶቿ ልማትን ለማፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ስለዚህ በኃይል ለመተባበር ዕድል ይሰጠናል፡፡ ሁለተኛ ይህ ግድብ ለታችኞቹ የተፋሰሱ ሃገሮች ዓመቱን በሙሉ “ሬጉሌትድ” የሆነ ውሀ የሚለቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተጨማሪ የልማት ዕድልን ይዞ የሚመጣ ነው፡፡ ስለዚህ ዓባይ እንዲሁም ደግሞ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግጭት ምንጭ፣ የንትርክ ምንጭ፣ ያለመግባባት ምንጭ ሳይሆን የትብብርና በጋራ ወደ ብልጽግና ለመጓዝ፣ ከድህነት ለመላቀቅ መሳሪያ ሆኖ የሚያገለግል የትብብር ፕሮጄክት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን ግድብ የምትመለከተው ለራሷ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ሃገሮችም የትብብር መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል የሚል ዕምነት አላት፡፡ ዓባይ የትብብር እንጂ ያለመግባባት ምንጭ ሊሆን አይገባም የሚል ዕምነት አለን፡፡ የግብጽ ወንድሞቼና እህቶቼ ይህንን በአግባቡ ይረዱታል ብዬ እገምታለሁ፡፡ አሁን በንትርክ የምናመጣው ለውጥ የለም፡፡ በትብብር ግን ብዙ ችግርን ልንሻገር እንችላለን፡፡ እንተባበር፤ ከተባበርን ውሀው ለሁላችንም ይጠቅማል፤ ለሁላችንም ይበቃል፡፡ በጋራ እንጠቀም በጋራ እንበልጽግ፣ በጋራ እንደግ የሚል መልዕክት አለኝ፡፡
አል- ዐይን፡- ኢትዮጵያና ኤርትራ የሰላም ስምምነት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ ይሁንና አሁንም ግልጽ የሆኑ ጉዳዮች የሉም እየተባለ ነው፡፡ እንዲያውም በፊት ከነበረው ሰላምም ጦርነትም የለም ከሚለው አዝማሚያ የተለየ አይደለም የሚሉ አሉ፡፡ አሁን ኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነታቸው ሚገለጸው እንዴት ነው?
አቶ ገዱ፡- ኢትዮጵያና ኤርትራ አሁን መልካም ጉርብትና ያላቸው ሃገሮች ናቸው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ይህ ማለት ኢትዮጵያና ኤርትራ ሊኖራቸው ከሚገባው ግንኙነት አኳያ መድረስ ባለበት ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ደግሞ ባለፉት 20 ዓመታት ከቆየበት ሁኔታ ስንመለከተው በእጅጉ መሻሻል ያሳየ ግንኙነት ነው፡፡ በጠላትነት ይፈላለጉ የነበሩ ሃገሮች አሁን በወዳጅነት የሚፈላለጉ ሃገሮች ናቸው፡፡ ሁለቱ ሃሮች መቼ ጦርነት ይጀመር ይሆን ተብሎ በስጋት ውስጥ ከነበሩበት ወጥተዋል፤ ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል፡፡ ግንኙነቱን ሙሉ ለሙሉ አቋርጠው ነበር አሁን ጀምረዋል፡፡ በሁለቱም ሀገራት ኤምባሲዎች ተከፍተዋል፤ አስመራ ላይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አዲስ አበባ ላይ ደግሞ የኤርትራ ኤምባሲ፡፡ አሁን በመሪዎች ደረጃ በበጎ ከመተያየት ያለፈ መልካም ግንኙነት በሁለቱ ሃገሮች መካከል ብቻ ሳይሆን በቀጣናው ስለሚኖረው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የወደፊት እንቅስቃሴ አብረው የሚሰሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ በመሬት የቀረ ቢሆንም በአየር (አውሮፕላን) አለ፡፡ እነዚህ መልካም ሁኔታዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያና ኤርትራ ሊኖራቸው ከሚገባው መልካም ግንኙነት አኳያ በምንመለከትበት ጊዜ ገና ብዙ መሰራት ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ የኢኮኖሚ ትስስርን ማጠናከር ይኖርብናል፤ የመሰረተ ልማት ትስስር መኖር አለበት፤ የንግድና የመሳሰሉት ግንኙነቶች መሻሻል መቻል አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ ግንኙነት ያለገደብ እንቅስቃሴ የሚደረግበት መሆን አለበት፡፡ እነዚህ፣ ወደፊት ይሄ ግንኙነት ተቋማዊ በሆነ መንገድ መሬት የረገጠ ሆኖ መካሄድ ይኖርበታል፡፡ ይሄ ገና ብዙ ያልተሰራ ስራ ነው፤ ተስፋ የምናደርገው ወደፊት በሁለቱም በኩል የጎደሉትን እየሞላን የተሻለ ሁኔታ ይኖራል የሚል ነው፡፡
አል- ዐይን፡-ጊዜ ወስደው ለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን፡፡
አቶ ገዱ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ፡፡