የዓረብ ሀገራት ስለ ህዳሴ ግድቡ ትክክለኛ መረጃ እንዲኖራቸው ያለመ ውይይት በባለሙያዎች ተካሂዷል
የዓረብ ሀገራት ስለ ህዳሴ ግድቡ ትክክለኛ መረጃ እንዲኖራቸው ያለመ ውይይት በባለሙያዎች ተካሂዷል
ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ተንታኞች፣ የህዝብ ተወካዮችን ምክር ቤት አባል እና የመገናኛ ብዙሃን አመራሮች ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ በምትገነባው ግድብ ዙሪያ በዓረብኛ ቋንቋ "ፍትሃዊና የጋራ ተጠቃሚነት" በሚል ርዕስ በአዲስ አበባ ውይይት አድርገዋል፡፡
የውይይቱ ዓላማ ለመካከለኛው ምስራቅና ለሌሎች ዓረብኛ ለሚናገሩ ህዝቦች ስለ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ትክክለኛውን መረጃ እንዲያውቁ ለማድረግ ነው ተብሏል፡፡
ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርና የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ናቸው፡፡
ውይይቱን የመሩት በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሚታተመው አል-ዓለም ጋዜጣ የቀድሞ አዘጋጅና የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባል አቶ ነስሩ አባ ጀበል፣ በግድቡ ዙሪያ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ትክክለኛ መረጃ እንዲኖረው ከእስካሁኑ የበለጠ ጥረት ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብን የተመለከቱ መረጃዎችና እውነታዎች ላይ ውይይት መደረጉ የተገለጸ ሲሆን መሰል ውይይቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ተብሏል፡፡
ውይይቱ የተዛቡ መረጃዎችን ለማስተካከልና ምን እየተሰራ እንደሆነ በትክክል ለማስገንዘብም ያስችላል ያሉት አቶ ነስሩ አባ ጀበል መሰል መድረኮች በስፋት መዘጋጀት አለባቸው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም እንደዚህ አይነት ሀገራዊ መድረኮችን በቀጣይ እንደሚያዘጋጅ ሰምተናል፡፡
የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ 9 ድፍን ዓመታት የተቆጠሩ ሲሆን እስካሁን ግንባታው ከ70 በመቶ በላይ ደርሷል፡፡ የግድቡን 9ኛ ዓመት በማስመልከት መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የግድቡ ግንባታ እስከመጪው ክረምት ተገባዶ የውሀ ሙሌቱ እንደሚጀመር ገልጸዋል፡፡
ምንም እንኳን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በግንባታ ሂደቱ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ቢኖረውም ግንባታው እንደሚቀጥል እና በክረምቱ ውሀ የመሙላት ሂደቱ እንደሚጀመር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተው አውስተዋል፡፡