በትግራይ እንደተደረገው ሁሉ በአማራ እና በአፋርም ተመሳሳይ አይነት የጣምራ ምርመራና ሪፖርት ይደረግ ይሆን ?
ህወሃት ሪፖርቱን ለምን “አልቀበልም “አለ ?
ኢሰመኮ ከተመድ ጋር በጣምራ የመብት ጥሰት ምርመራ ከመጀመሩ በፊት ህወሓትን ለማናገር ያደረገው ሙከራ ያገኘው ምላሽ ምን ነበር?
ከሰኔ 25 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ)ዋና ኮሚሽነር በመሆን እያገለገሉ ያሉት ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ቀደም ሲል በሂዩማን ራይትስ ዋች እና በአምነስቲ ኢንተርናሽናል በኃላፊነት ሰርተዋል፡፡ ኮሚሽነሩ ከሰሞኑ የጀርመን አፍሪካ ሽልማትን ተቀብለው ወደ ሀገር ቤት ተመልሰዋል፡፡ ተቋማቸው ኢሰመኮ በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት “ተከስተዋል” የተባሉ የመብት ጥሰቶችን ከተመድ የሰብዓዊ መብት ተቋም ጋር በጋራ በመሆን ያደረገውን ምርመራ ሪፖርት አድርጓል፡፡ አል ዐይን አማርኛ በዚህና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ ቆይታችንን እንዲትከታተሉ ጋብዘናል፡፡
አል ዐይን፡- ከሰሞኑ ሽልማት ተበርክቶልዎት ነበር፤ ሽልማቱን በተመለከተ ቢነግሩን ?
ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ፡- የጀርመን አፍሪካ ሽልማት የሚባለው በየዓመቱ ከአፍሪካ አንድ ሰው ሽልማት የሚሰጥበት ስርዓት ነው፡፡ እናም በተሰማሩበት ስራ ዘርፍ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሰዎች የሚሰጥ ሽልማት ነው፤ ከተጀመረ ወደ 30 ዓመት ገደማ ሆኖታል፡፡ እስከዛሬ ድረስ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ደርሶ የነበረ ቢሆንም ኢትዮጵያ አልደረሰም ነበር፡፡ ዘንድሮ በእኔና በተቋሜ አማካኝነት ወደ ተቋሙ ስለመጣና ስለስራችን የዚህ አይነት ዕውቅና ስለተሠጠን ደስ ብሎናል፡፡
አል ዐይን፡- ኢሰመኮ በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና በኦሮሚያ ክልል እንዲሁም በሌሎችም ቦታዎች የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን ሪፖርት ሲያደርግ ቆይቷል፤ ኮሚሽኑ ሪፖርት ማድረጉን ተከትሎ የመጣ ተጠያቂነት አለ ?
ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ፡- ልክ ነው የኢሰመኮ አንዱ ተግባሩ የመብት ጥሰቶችን ክትትል ማድረግ፤ መዘገብ ነውና በዚህ መሰረት አቅም በፈቀደ ብዙ ጥረት እናደርጋለን፤ የሰብዓዊ መብት ሁኔታው ላይ ለውጥ ለመፍጠር ግን የብዙ ነገሮችን ቅንጅትና የረጅም ጊዜ ራዕይ ይጠይቃል፡፡ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ለወደፊቱም ተመሳሳይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይከሰት ለማድረግ ነው እንደዚህ አይነት ሪፖርቶች የሚያስፈልጉት፡፡ እንዲሁም ደግሞ የተጎዱ ሰዎች እንዲካሱ፤ እንዲጠገኑና ህይወታቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ ማለት ነው፤ እና አልፎ አልፎ መጠነኛ የለውጥ ምልክቶች እናያለን በሌላ በኩል ግን ችግሩ በጣም ስር የሰደደ የብዙ ተቋሞችን ተሳትፎ የሚጠይቅ ስለሆነ በሚፈለገው መጠን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ለማየት ሊያስቸግር ይችል ይሆናል፤ ሁሉም አይነት ለውጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ ባታይም ግን የሥራውን አስፈላጊነት ያስቀረዋል ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም እንደዚሁ ውስብስብ የሆነ ጥልቅ የሆነ የሰብዓዊ መብት ችግር ያለባቸው ሀገራት ውስጥ የሰብዓዊ መብት ችግሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚፈታ አይደለም፡፡ እኛ አሁን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በአዲስ መልክ ኮሚሽኑን አጠናክረን ስራ ከጀመርን እንኳ ገና ሁለተኛ ዓመት ላይ ነው ያለነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ ቀውስ በሙሉ በዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ አምጥቷል ለማለት ያስቸግራል፤ ይልቁንም አንዳንድ ጊዜ የበለጠ የተባባሱ ሁኔታዎች እናያለን ፤ ስለዚህ የረጅም ጊዜ ራዕይ መያዝ ያስፈልጋል፤ ለረጅም ጊዜ ለውጥ ደግሞ የሚስፈልጉት መሰረት ድንጋዮች መጣለቸውን ማየት ያስፈልጋል፤ በዚህ መንፈስ ነው የምንሰራው ግን በዚህ ውስጥም ቢሆን በተወሰነ መጠን ውጤት ማየት ጀምረናል፤
አል ዐይን፡- በአንድ ወቅት በወጣ ሪፖርታችሁ ላይ የኦሮሚያ ክልል የሥራ ኃላፊዎች ቅሬታ አንስተው ነበር፤ ምክንያቱ ምን ነበር ?
ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ፡- የክልሉ ኃላፊዎች ቅሬታቸው በተወሰነ መጠን በክልሉ ውስጥ ያለውን የጸጥታ አደጋ መጠን መሰረት በማድረግ እደሚታወቀው በተለያዩ ኦሮሚያ ክልል የታጠቀ ቡድን አሁን ደግሞ በሀገሪቱ ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ቡድን ማለት ነው በጣም በተደጋጋሚ ጥቃት የሚያደርግ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህም ደግሞ በጣም ብዙ ጉዳት የደረሰ መሆኑ አይካድም፤ እኛም በሪፖርታችን ላይ ይህንን በግልጽ እናመለክታለን፤ እና እንደምረዳው የተወሰኑ የክልሉ ኃላፊዎች የመከራከሪያ ነጥባቸው የጸጥታ ኃላፊዎቹ የገጠማቸው ፈተና ቀላል ስላልሆነ ይህንን ለመቋቋም በሚወስዱት እርምጃ ወስጥ የሚከሰቱ ችግሮች አልፎ አልፎ ቢኖሩም ይህንን መረዳት ይገባል የሚል ስሜት እንዳለው እረዳለሁኝ እና በተወሰነ መጠን እንረዳዋለን ፤ በሌላ በኩል ግን እንዲህ አይነት የታጠቀ ቡድን ብዙ ጉዳትና ጥፋት እያደረሰ ያለበት አካባቢ ቢሆንም የህግ ማስከበር ስራ ሁል ጊዜ በጣም ህጋዊ በሆነ መንገድ እስካልተመራ ድረስ ለበለጠ ችግር መባባስ ምክንያት ሊሆን ስለሚችል ሊወሰዱ የሚችሉ ጥንቃቄዎችን ነው ለማሳሰብ የምንወደው፤ በዚህ ደግሞ ሰፋ ባለ አነጋገር መግባባት አለን ብዬ አስባለሁ፤
አል ዐይን፡- በጦርነቱ ምክንያት “ተፈጽመዋል” የተባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ከተመድ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ጋር በጋራ መርምራችኋል፤ ምርመራውን ብዙዎች ሲቀበሉት ህወሃት አልተቀበለም ለምን ይመስልዋታል ?
ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ፡- ህወሃት ሪፖርቱን አልቀበልም ያለው ያው ከመነሻው ጀምሮ በሂደቱ ውስጥም አልሳተፍም በማለትም ጭምር ነበር፡፡ የምርመራ ሂደቱ ላይም ሳይሳተፍ የቀረው የጣምራ ሂደቱን አልቀበልም በማለቱ ነበር፡፡ ለዚህም ምክንያት ያደረገው በተለይ በእኛ ኮሚሽን ላይ እምነት የለኝም በሚል ነው፤ አሳዛኝ አጋጣሚ ነው ግን ሪፖርቱ ከወጣ በኋላ ደግሞ የሪፖርቱን ሚዘናዊነት ተመልክተው ይቀበሉታል የሚል ተስፋ ነበረኝ፤ አሁንም ምናልባት በጥሞና ሪፖርቱን ካነበቡት ሊቀበሉ የማይችሉበት ምክንያት እኔ አለ ብዬ አላምንም እና ሪፖርቱን በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑትን ወገኖች በሙሉ ሊቀበሉት ይገባል ብዬ አስባለሁ፡፡ እሳካሁን ሪፖርቱን አንቀበልም ብለው ያሳወቁት የኤርትራ መንግስት እና ህወሃት ናቸው፡፡ ነገር ግን የማይቀበሉበት አሳማኝ ምክንያት አላደመጥንም እስካሁን ፤እርግጥ ቅሬታዎች እንዳሉ እረዳለሁ፤ ከቅሬታዎች ውስጥ አንዱ ሪፖርቱ ምርመራ ሊደረግባቸው የሚገባቸውን ቦታዎች በሙሉ አልሸፈነም የሚል ነው፤ ይህንን ደግሞ እርግጥ ወን ትክክል ነው፤ እኛም በሪፖርቱ ላይ አመልክተናል፤ ለመሸፈን አልቻልንም ግን በተወሰነ መጠን እነዛን ቦታዎች መሸፈን ያልቻልነው አንደኛ በአካባቢው ባለው ጸጥታ ችግር ሁለተኛ ደግሞ ህወሃት እራሱ ለምርመራ ሂደቱ ተባባሪ ባለመሆኑ የተነሳ ነው፡፡ ሌላው ነጥብ ደግሞ ይህ ሪፖርት ሁሉንም ቦታዎች ባይሸፍንም ወደፊት በሚደረጉ የምርመራ ስራዎች ግን መሸፈናቸው አይቀርም፤ እስካሁን ድረስ የደረሰውን ሰብዓዊ መብት ሁኔታ በሚመለከት ግን ከዚህ ሪፖርት የበለጠ የተሟላ እና በቦታው ላይ በመገኘት የተደረገ ምርመራ ስራ ስለሌለ ይህንን ሪፖርት ላለመቀበል ምንም ምክንያት መሆን አለበት ብዬ አላምንም እና አሁንም ቢሆን ህወሃትም ሆነ ደጋፊዎቻቸው ይህንን ሪፖርት ይቀበሉታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
አል ዐይን፡- የጣምራ ምርመራው አሁን ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች ይቀጥል ይሆን ?
ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር ) ፡- የጣምራ ምርመራው እስከተከናወነበት ድረስ ያለውን ወቅት ከሸፈንን በኋላ ከዛ በኋላ ያለውን ጊዜ በሚመለከት ኢሰመኮ እንዲሁም የተመድ በየተቋሞቻችን አማካኝነት የምርመራና የክትትል ስራችንን ቀጥለናል፡፡ ኢሰመኮ የተወሰኑ የአማራ ክልል አካባቢዎች የተከሰተውን ሁኔታ በሚመለከትም አጠር ያለ ሪፖርትም አውጥተናል፤ ነገር ግን ኢሰመኮ እና የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ጽ/ቤት ምናልባት አሁንም በዚህ አካባቢም የጣምራ ምርመራ እና ሪፖርት ለማካሄድ የምንችልበት ሁኔታ እንዳለ ስለተረዳን ቢያንስ ምክክርና ሃሳብ መቀያየር ጀምረናል፡፡
አል ዐይን፡- በትግራይ በነበረው ጦርነት “በርካቶች የሰብዓዊ መብቶች ስለተጣሱ ምርመራ ሊደረግ ይገባል “ የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያሰሙ ነበር፤ አሁን ጦርነቱ ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች ከተስፋፋ በኋላ “ምርመራ ይደረግ የሚል ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ አይነሳም “ ይባላል፡፡ ይህ ምን ያህል እውነት ነው ?
ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ፡- አንደኛ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ጽ/ቤት በራሳቸው አማካኝነት ክትትል ሲያደርጉ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ሁለተኛ እኛም ራሳችን ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ነገር ግን እንደተባለው በሌሎች ሁኔታዎች ላይ ተመሳሳይ ምርመራ እንዲካሄድ ሲደረግ በነበረው ዓለም አቀፍ ጥሪ መጠን በዚህ ላይ አተኩሮ የተደረገ የተለየ ጥሪ ባይኖርም ነገር ግን ግጭቱ ወደ አማራና አፋር ከተስፋፋ በኋላ ያለው ሁኔታ የዋናው ግጭት አካል አድርጎ የመመልከት ሁኔታ አለ፤ የዋናው ግጭት የመስፋፋት መገለጫዎች ናቸው ስለዚህ ግጭቱ አሁን እና ውጤቱ በትግራይ ክልል ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ወደ አጎራባች ክልሎችም የተስፋፋ መሆኑንና በአጠቃላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተው ግጭት ተጨማሪ ምርመራም የሚያስፈልገው መሆኑንም ከተለያዩ ወገኖች ይደመጣል፤ እኛም ይህንኑ ሥራችንን እንቀጥላለን፡፡
አል ዐይን፡- ስለዚህ በአማራ እና አፋር ክልሎች የመብት ጥሰቶችን በተመለከተ በትግራይ እንደተደረገው ሁሉ ጣምራ ምርመራ ሊደረግ ይችላል ?
ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር )፡- እንግዲህ ገና በመነጋገር ላይ ነን፤ በመነጋገር ላይ ስለሆንን እና የመጨረሻ ስምምነት ላይ ስላልደረስን እርግጠኛ መልስ አሁን ለመስጠት አልችልም፡፡ ግን ተመሳሳይ አይነት የጣምራ ምርመራና ሪፖርት ለማከናወን ግን ከተመድ ጋር ምክክር ተጀምሯል፡፡
አል ዐይን፡- ምክክሩ የተጀመረው ከተመድ የሰብዓዊ መብት ጽ/ቤት ጋር ነው ?
ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ፡- አዎ
አል ዐይን፡- የአፍሪካ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምርመራ አደርጋለሁ ብሎ ነበር፤ ምን ላይ ደረሰ ?
ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር ) ፡- የአፍሪካ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እንደዚሁ ምርመራ እያካሄደ የነበረ መሆኑን የገለጸ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግስት ካደረኩለት ግብዣ ውጭ ለብቻው በተናጠል የሚያካሂደው ምርመራ ስራ ነው በማለቱ የተነሳ በመንግስት ዕውቅና አልተሰጠውም፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ደጋግሞ ለአፍሪካ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጥሪ አድርጎ የነበረው ልክ ከተመድ ጋር እንደተደረገው ከሀገራዊው ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋም ጋር በመቀናጀት በጣምራ በአንድነት እንዲሰራ የሚል ግብዣ ነበር የቀረበት፡፡ የአፍሪካ ኮሚሽን ግን በዚህ መልክ ለመስራት ፈቃደኛ ባለመሆኑ የተነሳ እስካሁንም ድረስ በመንግስትና በኮሚሽኑ መካከል አለመግባባት መኖሩን መንግስትም ደግሞ ለምርመራው ዕውቅና ያልሰጠ መሆኑን አውቃለሁ፡፡
አል ዐይን፡- በምርመራዎቹና በሌሎች ስራዎቻችሁ ላይ ከመንግስት አካላት ጫና ነበረባችሁ ?
ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር ) ፡- ምንም አልነበረም፡፡ በእውነቱ በዚህ ከተመድ ጋር ባደረግነው የጣምራ ምርመራ ስራም ብቻ ሳይሆን ኢሰመኮ ከዚህ ከአዲሱ የለውጥ ምዕራፍ ወዲህ በስራችን ላይ ከየትኛውም የመንግስት አካል ጣልቃ ገብነትም፤ ጫናም የለም፤ ቢኖርም አንቀበልም፡፡ ነጻ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋም እንዲሆን ታስቦ የተቋቋመ ተቋም ነው፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዚህ መልክ ለመስራት ጥሩ ፣በጎ እርምጃዎች ጀምረናል፡፡ ስለዚህ በዚህ ስራችን ውስጥ የመንግስትን ጣልቃ ገብነት እና ጫና ፈጽሞ አንቀበልም፡፡ ግን የዚህ አይነት ጫና እና ጣልቃ ገብነትም አልገጠመንም፡፡ ይህ ማለት ግን በስራችን ውስጥ እክል አይገጥመንም ማለት አይደለም፤ በጣም በርካታ እክሎች ይገጥሙናል፤ የታሰሩ ሰዎች የሚገኙበትን ቦታ ሄደን ለመጎብኘት እንቅፋት ከማጋጠም ጀምሮ የሎጀስቲክስም፣ የኦፕሬሽንም፣ የጸጥታም አንዳንድ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች ውስጥም ተገቢውን ትብብርና እገዛ ያለማድረግም ችግር ይገጥመናል፡፡ ይህ ማለት ግን በሁሉም መንግስታዊ ተቋሞች እንዲህ አይነት ችግር ይገጥመናል ማለት አይደለም፡፡ በርካታ ፖሊስ ጣቢያዎች፣ ማረሚያ ቤቶች ትብብር ያደርጋሉ፤ እንሄዳለን፣ እንጎበኛለን፣ የታሰሩ ሰዎችን እናያለን፣ እንዲሁም በርከታ የመንግስት መስሪያ ቤቶችም በራቸውን ክፍት አድርገው ያነጋግሩናል፤ መረጃ ይሰጡናል፣ ስለዚህ ችግር ቢኖርም፤ ችግሩን እየተቋቋምን ወይም ደግሞ ችግሩን ለዘለቄታው ለመፍታት ጥረት እያደረግን ስራችንን እንሰራለን፡፡
አል ዐይን፡- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ በተለየ ሁኔታ የትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ እስር እየተደረገ መሆኑ ይገለጻል፡፡ ኢሰመኮ ለዚህ አስተያየት ምን ምላሽ አለው ?
ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር )፡- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ ጊዜ ጀምሮ የተከሰተውን እስር ሁኔታ በጣም በቅርበት ስንከታተል ቆይተናል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታስረዋል፡፡ ከታሰሩት ሰዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ የትግራይ ተወላጆች ናቸው፤ እርግጥ ሌሎችም ሰዎች የታሰሩ አሉ፤ ግን አብዛኛዎቹ ታሳሪዎች የትግራይ ተወላጆች መሆናቸውን መካድ አይቻልም፡፡ የእስር ሁኔታው አሳሳቢ ነው፤ በጣም በርካታ ሰዎች በጣም አነስተኛ በሆነና የተጨናነቀ ቦታ እና በቂ አገልግሎት በሌለበት ቦታ ታስረው ይገኛሉ፡፡ ከታሰሩት ሰዎች ውስጥ ዕድሜያቸው የገፋ እና የህክምና ክትትል የሚያስፈልጋቸው ሰዎችም እንዳሉ ተመልክተናል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ የምናነጋግራቸው የመንግስት ኃላፊዎችና የህግ አስከባሪ አካሎች እስሩ የብሔር ማንነትን መሰረት ያደረገ አይደለም በማለት ያስረዱናል፡፡ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንጻር ያስፈለገበትን ምክንያት ያስረዱናል፤ በአዋጁ መሰረት ምክንያታዊ ጥርጣሬ ሲኖር ሰዎች ሊታሰሩ እንደሚችሉ በአዋጁ የተመለከተ ቢሆንም አንዳንዱ እስር ግን በምክንያታዊ ጥርጣሬ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ግን ያጠራጥረናል፡፡ ስለሆነም የበለጠ ትኩረት ይሻል፤ የበለጠ ምርመራ ይሻል፤ በተለይ ህክምና የሚያስፈልጋቸውን ሰዎችና ዕድሜያቸው የገፋ ሰዎችም ሁኔታ አሳሳቢ ስለሆነ የበለጠ ትኩረት ይሻል ብለን እናምናለን፡፡ እርግጥ አሁን ሀገሪቱ ያለችበትን የብሔራዊ ጸጥታ ደህንነት ስጋት ብንረዳም በሌላ በኩል ግን ደግሞ የዜጎች አያያዝ እና የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ሁኔታ የዛኑ ያህል ደግሞ ያሳስበናል፡፡ ስለዚህ የሕግ አስከባሪ አካሎቹ እየወሰዱ ያሉትን እርምጃ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት ሕጋዊ መሰረት ያለው መሆኑን ብንረዳም ግን አዋጁ ደግሞ ለአቢዩዝ እንዳይዳረግ ተገቢ ላልሆነ አሰራር እንዳይጋለጥ ጥንቃቄ በጣም ያስፈልጋል፡፡ አላግባብ የታሰሩ ሰዎች ሊኖሩ መቻላቸው ሊካድ አይገባም፤ ስለዚህ ጉዳዩ በጣም ትኩረት ይሻል፤ እልባትም ይሻል፣ እና በዚህ መንፈስ መከታተላችንንና መወያየታችንን ቀጥለናል እና ሁኔታው እየተሻሻለ ይመጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
አል ዐይን፡- ህወሃት፤ እርስዎ ለመንግስት እንደሚያዳሉ ይገልጻል፤ ሪፖርቱንም አልቀበልም ያለው እርስዎ በመንግስት የተሾሙ በመሆንዎና ለመንግስት ሊያዳሉ ይችላሉ በሚል ነው፡፡ በዚህ ላይ ምን ምላሽ አለዎት ?
ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ነጻ ተቋሞች ልምድ አልነበረንም፡፡ በፖለቲካ ታሪካችን እና በመንግስት የሚቋቋሙ መስሪያ ቤቶች ነጻ ሆነው እንዲቋቋሙ ቢፈለግም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ግን መስሪያ ቤቶች በሙሉ በመንግስት የፖለቲካ ተጽዕኖ ስር ወድቀው የነበሩበት ታሪካችን የቅርብ ጊዜ ትዝታ ስለሆነ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶችን በሙሉ በጥርጣሬ የማየት ዝንባሌ ሊኖር ይችላል፡፡ ምናልባት ደግሞ ይሄ በኢህአዴግ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ፤ራሳቸው ምናልባት የኢህአዴግ ሰዎች ሲያደርጉት የነበረው አሰራር ስለሆነ በዛ መንፈስ አሁንም መንግስታዊ ተቋሞችን በሙሉ በጥርጣሬ የማየት ሊኖር እንደሚችል እረዳለሁኝና ህብረተሰቡ በነጻነት በተቋቋሙ ተቋሞች ላይ ያለው እምነት በጊዜ ሂደት እየጨመረ የሚመጣ መሆኑን እረዳለሁ፤ በዚህ መሰረትም በኢሰመኮ ላይ በሀገር ውስጥም በውጭም ያለው እምነት በጣም እያደገ የመጣ ለመሆኑ በርካታ ምልክቶች አሉ ብዬ አምናለሁኝ፡፡ ነገር ግን ሌላው የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ በጣም እጅግ የተካረረና በብሔር መነጽር የሚታይ ነውና በዚህ ውስጥ ጉዳዩን ከፖለቲካ መነጽር የሚያዩት፤ ከብሔር መነጽር የሚመለከቱት፤ ወንድሞችና እህቶች ይኖራሉ፤ ስለሆነም የበኩላቸው አስተያየት ይኖራል፤ የበኩላቸው ትችት ይኖራል፤ የበኩላቸው ጥርጣሬ ይኖራል እነዚህን ሁሉ ነገሮች ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መሰረት አደምጠዋለሁ፣ አከብረዋለሁ፡፡ ነገር ግን የሚሰጡት ትችቶችና አስተያየቶች በሙሉ ትክክል ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ይህንን አድማጭ ሁሉንም አስተያየት እያደመጠ፣ እየተመለከተ መመዘንና መፍረድ ይኖርበታልና ብዙ ምክንያታዊ ያልሆኑ ትችቶች እንዳሉ በጣም ግልጽ ይመስለኛል፤ በተወሰነ መጠንም ከጥላቻ የሚመነጭ ትችትም እንዳለ መገንዘብ ይቻላል፤ በተወሰነ መጠንም ለማራመድ ከምትፈልገው የፖለቲካ አስተሳሰብ አንጻር የምትይዘው የፖለቲካ አቋምና የምትሰነዝረው ትችት ይኖራል፤ ስለዚህ የነዚህ ሁሉ ነገሮች መገለጫ ነው፤ በመጨረሻ ላይ ግን ወሳኝ የሚሆነው ነገር የእያንዳንዱ ተቋም የሚታይ የሚጨበጥ ስራ ነውና በዛ ነው መመዘን ያለበትና በዚህ መልክ መታየት ያለበት ነው የሚመስለኝ፡፡ሌላው ኢሰመኮ በአዲስ መልክ እንዲቋቋም ከተደረገ በኋላ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች የሚሾሙት አንደኛ በምክር ቤት ነው፤ ሁለተኛ እንደከዚህ በፊቱ አሰራር ሳይሆን የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች በሙሉ የፖለቲካ ፓርቲ አባል እንዳይሆኑ በአዋጁ ተከልክሏል፡፡ ይሄ ከዚህ በፊት ከነበረው አሰራር የተለየ ነው፤ በቀድሞው የኢህአዴግ አስተዳደር የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች የፖለቲካ ፓርቲ አባል የነበሩ ሰዎች ናቸው፤ አሁን ግን በአዲሱ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ይሄ በግልጽ ተከልክሏል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን አይገባም፣ የኮሚሽኑን ነጻነት ለማረጋገጥም የተወሰዱ ሌሎች በርካታ እርምጃዎች አሉ፤ በተለይ የሰው ሃብት፣ የፋይናስና የበጀት አስተዳደር ነጻነቱን ለመጠበቅ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በነዚህ አይነት ሕጋዊ መሰረት እውነተኛ ነጻ፣ ጠንካራ የሆነ ሰብዓዊ መብት ተቋም እየተፈጠረ ስለሆነ ይሄ እንደበጎ እርምጃ የሚታይ ነው ብዬ አምናለሁኝ፡፡
አል ዐይን፡- ህወሃት፤ በእርስዎ ላይ ጥያቄ የሚያነሳውና የሚመሩት ተቋምም ገለልተኛ እንዳልሆነ የሚገልጸው ቀደም ብሎ ይሰሩባቸው ከነበሩ ተቋሞች ጋር በተያያዘ ሊሆን ይችላል ?
ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፡- እሱ ደግሞ ሌላ የሚገርም ታሪክ ይኖረዋል፤ ምክንያቱም እኔ ወደዚህ ስራ ከመምጣቴ በፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ የሰብዓዊ መብት ተቋሞች ውስጥ በተለይ ሂዩማን ራይትስ ዋች እና አምነስቲ ኢንተርናሽናልናቻ ሁለት የታወቁ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋሞች እና በሁለቱም ውስጥ አገልግያለሁ በኃላፊነት ደረጃ እና እዛ እሰራበት በነበረበት ወቅት ደግሞ ኢህአዴግ ሲያወግዝ ያነበረው ኢህአዴግም ፣ ህወሃትም ሲያወግዙ የነበሩት ደግሞ እነዚህን ተቋሞች ነው፤ እነዚህ ተቋሞች ትክክለኛ ተቋሞች አይደሉም በሚል ነው፤ አሁን ደግሞ እነሱን ተቋሞች ነው እንደማስረጃ ለመጥቀስ የሚሞክሩት ስለዚህ ይህ የሚያመለክትህ ምንድው ብዙ ጊዜ የፖለቲካ ቡድኖች ወይም አንድ የሆነ የፖለቲካ አጀንዳ ማራመድ የሚፈልጉ ቡድኖች ወይም ድርጅቶች እውነተኛ ምክንያታቸው የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ሳይሆን የፖለቲካ አጀንዳው ወይም የፖለቲከ ጥቅሙ ይሆናል ማለት ነው ስለሆነም በመርህ ላይ ያልተመሰረተ ትችት ይሆናል ማለት ነው፡፡
የሰብዓዊ መብት ምርመራ ስራው ይጠቅመኛል ብለህ ስታስብ ትጠቀምበታለህ፤ የፖለቲካ ጥቅምህን ለማራመድ ይጎዳኛል ብለህ ስታስብ ደግሞ የፖለቲካ ጥቃትና ትችት ትሰነዝርበታለህ ፤ ስለዚህ በመርህ ላይ ያልተመሰረተ ትቸት ይናሆናል ማለት ነው እና በእኔ አስተያየት ድሮም በነዛ አይነት ተቋሞች ውሰጥ ስሰራ የነበረው ስራ ትክክለኛ ሰብዓዊ መብት ስራ ነው እነዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ የሰብዓዊ መብት ተቋሞች ናቸው አሁንም ደግሞ በዚህ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋም አማካኝነትም የምንሰራው በተመሳሳይ ምርሆች ላይ የተመሰረተ የሰብዓዊ መብት ስራ ነው፤
አል ዐይን፡- ህወሃት፤ እርስዎን በተለያየ አማራጭ ለማግኘት የቻለበት መንገድ አለ ?
ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፡- አይ የለም፤ ግን እኛ ይህንን ስራ በተለይ ከተመድ ጋር በጣምራ የምናካሂደው የምርመራ ስራ ለማሄድ ግን በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ወገኖችን ማነጋገር ያስፈልግ ስለነበር ህወሃትም ለምርመራው ስራው ትብብር እንዲያደርግና ለጥያቄዎቻችንም ምላሽ እንዲሰጠን ለማነጋገር ኮሚሽናችንና የተመድ ጽ/ቤት በአንድነት ሆነን ጥሪ አቅርበንላቸው ነበረ፤ ግን ለመተባባር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡
አል ዐይን፡- ከጦርነቱ ውጭ ባሉቦታዎች ያለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ተሻሽሏል ወይስ አልተሻሻለም ?
ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር ) ፡- ጦርነቱ የምንለው በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ግጭት አንደኛው ነው በሌላ በኩል ግን በሰሜን ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎችም ላይ ግጭት ያለባቸው አካባቢዎች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ምናልባት በሁሉም ክልሎች በሚባል ደረጃ አመጽ የተቀላቀለበት ግጭት አለ እና በዚህ ግጭት ውስጥ ደግሞ የሚከሰቱ አደጋዎች ከፍተኛው የሰብዓዊ መብት ጥሰት መገለጫዎች እነሱ ናቸው፡፡
ለሰው ህይወት መጥፋት፣ ለአካል ጉድለት መድረስ፣ ለንብረት መውደም፣ ለመፈናቀል ምክንየት የሚሆነው በአብዛኛው ከግጭት ጋር በተያያዘ የሚከሰተው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነውና ይሄ አሁንም የተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ አሳሳቢ ችግር ነው፡፡በሌላ በኩል ግን በዚህ በአዲስ የፖለቲላ ምዕራፍ በአንድ በኩል ጥሩ እርምጃዎች ታይተዋል፡፡ በተለይ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ በማድረግ ከዚህ በፊት የነበሩ ጨቋኝ ሕጎች እንዲሻሻሉ፣ እንዲሻሩ በማድረግና በአዳዲስ ህጎች እንዲተኩ በማድረግ፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በነጻነት እንዲሰሩ በማድረግ መፍቀድ፤ ሚዲያ በጣም በተሻሻለ ሁኔታ በነጻነት ስሜት እንዲሰራ በማድረግ የተወሰዱት እርምጃዎች ሁሉ በጣም የሚያበረታቱ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ግን ከችግር ነጻ ነው ማለት አይደለም፤ በሚዲያም ላይ አልፎ አልፎ ችግር ያጋጥማል፤ የሚዲያ ሰራተኞች ላይ ችግር ያጋጥማል፤ አሁንም አላግባብ የታሰሩ ሰዎች አሉ፤ አሁንም የዋስትና መብታቸው ተፈቅዶ ግን የዋስትና መብታቸው ሳይከበር እስር ላይ ያሉ ሰዎች አሉ፤ አልፎ አልፎ ተገቢ ያልሆነ የእስር አያያዝም ያጋጥመናል፡፡ ስለዚህ እንደዚህ የተደበላለቀ መልክ አለቀው እና በአንድ በኩል የመሻሻል ተስፋ ቢታይም በሌላ በኩል ደግሞ አሳሳቢ የሆነ የሰብዓዊ መብት ችግር ያለ መሆኑ ይታወቃል፤
አል ዐይን፡- እርስዎ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ነዎት በእርስዎ እይታ ኢትዮጵያ አሁን ምንአይነት ሁኔታ ላይ ናት ?
ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፡- ኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ የሆነ የፖለቲካ የሰብዓዊ እና የሰብዓዊ መብት ቀውስ ውስጥ ያለች መሆኑ አይካድም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ምንም እንኳ ይህንን የመሰለ ከፍተኛ ፈተናና ቀውስ የገጠመን ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ግን ሀገራቸውን ይወዳሉ፤ ሀገራቸው ከዚህ ችግር ወጥታ ወደፊት ስትራመድ ማየት ይፈልጋሉ በዚህ መንፈስ ደግሞ የመተባበርና አብሮ የመስራት ስሜትም ይታያል፤ ስለዚህ ከባድ ፈተና የገጠመን ቢሆንም ተስፋ ግን ደግሞ የሚያስቆርጥ አይደለም፡፡ ይህንን ችግር ሀገሪቱ ተቋቁማ ኢትዮጵያውያን ይህንን ችግር አልፈው በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል ደግሞ የተፈጠረውን ጥሩ ያልሆነ ስሜት እና ይሄ ማህበራዊ ትስስርን የጎዳው ችግርም ድኖ፤ ቁስሉ ሽሮ በአንድነት መንፈስ ኢትዮጵያውያን ወደፊት ለመራመድ ዕድል አሁንም አለ፡፡ በጣም አልፎአልፎ የችግሩ መጠን አግዝፈን ስናየው መፍትሄ የሌለው ሊመስል ይችላል እንጅ መፍትሄ የሌለው ችግር አይደለም ኢትዮጵያ የገጠማት፡፡ ይህንን ችግር ኢትዮጵያውያን ተቋቁመው ወደፊት ለመራመድ ዕድል አለ ብዬ አስባለሁ፡፡
አል ዐይን፡- በጣም አመሰግናለሁ፡፡
ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡