የደምቢዶሎው ተጠርጣሪ ከህግ ውጭ በአስደንጋጭ ሁኔታ መገደሉን ኢሰመኮ አስታወቀ
ጉዳዩ በአስቸኳይ ተመርምሮ በአጥፊዎች ላይ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድም ጠይቋል
ኢሰመኮ ተጠርጣሪው አማኑኤል ወንድሙ በሚያስደነግጥ ሁኔታ በፀጥታ ኃይሎች በአደባባይ መገደሉን አስታውቋል
በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን አማኑኤል ወንድሙ የተባለ የወንጀል ተጠርጣሪ በአስደንጋጭ ሁኔታ በፀጥታ ኃይሎች በአደባባይ መገደሉን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡
ኢሰመኮ ተጠርጣሪው ትናንት ማክሰኞ ጥር 3 ቀን 2013 ዓ/ም ከህግ አግባብ ውጭ በሆነ አስደንጋጭ ሁኔታ ህዝብ እያየ በአደባባይ መገደሉን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የወጣት አማኑኤል ወንድሙ ግድያ ጉዳይ ትናንት የማህበራዊ ሚዲያዎች መነጋገሪያ ሆኖ ነው ያመሸው፡፡
ወጣቱ ከፍተኛ ድብደባ እና እንግልት እንደደረሰበት የሚያሳዩ የምስል እና የተንቀሳቃሽ ምስል (ቪዲዮ) ማስረጃዎችም ሲዘዋወሩ ነበር፡፡
በቪዲዮዎቹ ወጣቱ የፊጥኝ (ወደ ኋላ) ታስሮም ይስተዋላል፡፡
ከህግ ውጭ የሚደረጉ የትኞቹንም ዓይነት ግድያዎች አወግዛለሁ ያለው ኢሰመኮም ሁሉም ህግ የማስከበር ዘመቻዎች በህግ አግባብ እንዲፈጸሙ አሳስቧል፡፡
ግድያዎቹ በህግ የበላይነት ላይ እምነትን ከማሳጣትም በላይ የተገኙ ውጤቶችን እንደሚቀለብሱም ነው ኢሰመኮ ያስታወቀው፡፡
በመሆኑም የአማኑኤል ወንድሙ ግድያ ጉዳይ በአስቸኳይ ተመርምሮ በአጥፊዎች ላይ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቋል፡፡
ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተልኩ ነው ያለም ሲሆን የሚደርስበትን እንደሚያሳውቅ ገልጿል፡፡
ኢሰመኮ ከአሁን ቀደምም በኦሮሚያ ክልል ባለው የመብት አያያዝ በተለይም የእስረኞች አያያዝ ሁኔታ መስጋቱን በመግለጫ አስታውቋል፡፡
ሆኖም የክልሉ መንግስት “መግለጫዎቹ ሚዛዊነት የሚጎድላቸው ናቸው” ሲል ኮሚሽኑ አለ ያለውን የመብት አያያዝ ችግር ማስተባበሉ የሚታወስ ነው፡፡