በአማራ፣ ኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መቀጠላቸውን ኢሰመኮ ገለጸ
ኢሰመኮ በሶስቱ ክልሎች ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ብሏል
በኦሮሚያ አርሲ ዞን 11 የአንድ ቤተሰብ አባላት መገደላቸውን ኢሰመኮ ገልጿል
በአማራ፣ ኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መቀጠላቸውን ኢሰመኮ ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ፣ኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል፡፡
እንደ ኢሰመኮ ሪፖርት ከሆነ በአማራ ክልል በአዊ ብሔረሰብ ዞን፣ በአየሁ ጓጉሳ ወረዳ እና በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ቡሬ ዙሪያ ወረዳ፤ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ አሶሳ ዞን፣ ኦዳ ብልድግሉ ወረዳ፤ በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል፣ በአርሲ ዞን፣ ሸርካ ወረዳ እና በቄለም ወለጋ ዞን፣ ጊዳሚ ወረዳ በሲቪል ሰዎች ላይ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
በአማራ ክልል፣ በአዊ ብሔረሰብ ዞን አስተዳደር፣ በአየሁ ጓጉሳ ወረዳ፣ አምበላ ቀበሌ እና በዚገም ወረዳ ሶሪት ቀበሌ ከጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ቀናት በተፈጠረው ብሔር ተኮር ግጭት ሞት እና የአካል ጉዳት እንዲሁም በኢንቨስትመንት ቦታዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።
እንዲሁም በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ቡሬ ዙሪያ ወረዳ፣ ፈጣም ሰንቶም እና በቆጣቦ ቀበሌዎች ጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. እና በኅዳር 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ኢመደበኛ የአማራ ታጣቂዎች መሆናቸው የተገለጸ ቡድኖች በሰነዘሩት ብሔር ተኮር ጥቃት እና ይህንኑ ተከትሎ በተፈጠረው ግጭት በርካታ ሰዎች ላይ የሞት፣ የአካልና የንብረት ጉዳት መድረሱንም ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ላይ ገልጿል፡፡
በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ነዋሪዎች ተፈናቅለው በቡሬ ዙሪያ ወረዳ በሚገኙ አጎራባች ቀበሌዎች እና ወደ ኦሮሚያ ክልል ከመሰደዳቸው ባለፈ የቀንድ ከብቶችም ተዘርፈዋል ተብሏል።
ኮሚሽኑ አክሎም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ አሶሳ ዞን፣ ኦዳ ብልድግሉ ወረዳ ሥር በሚገኙ ቤልሚሊ፣ አልከሻፊ እና ቤላደሩ ቀበሌዎች በሚኖሩ የቤኒሻንጉል ብሔር ተወላጆች እና አብረው በሚኖሩት የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ላይ ኅዳር 19 ቀን 2016 ዓ.ም. ከንጋቱ 11፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀኑ 5፡00 ሰዓት አካባቢ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ ኦነግ-ሸኔ) ታጣቂ ቡድን አባላት ጥቃት ተፈጽሟል ብሏል፡፡
በዚህ ጥቃት 17 ሰዎች መገደላቸውን፣ አንድ ሽማግሌ ታፍነው መወሰዳቸውን፣ በ7 (ሰባት) ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ሌሎች ነዋሪዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል ተብሏል፤፤
እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን፣ ሸርካ ወረዳ ኅዳር 13 ቀን 2016 ዓ.ም. በጢጆ ለቡ ቀበሌ በግምት ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት በኋላ ማንነታቸው በውል ያልተለየ ታጣቂዎች በፈጸሙት ብሔር/ማንነት ተኮር ጥቃት 7 የአንድ ቤተሰብ አባላት እና ሦስት ጎረቤቶቻቸው ጨምሮ በአጠቃላይ 10 ሰዎችን እንደገደሉም ኢሰመኮ በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በዚያው ዕለት ታጣቂዎቹ በሶሌ ዲገሉ ቀበሌ ቢያንስ 12 ሲቪል ሰዎችን መግደላቸውን የሚያመላክቱ መረጃዎችና ማስረጃዎች ኮሚሽኑ አሰባስቧል፡፡
በሲቪል ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎች እና እስሮች "እጅግ አሳሳቢ" መሆናቸውን ኢሰመኮ ገለጸ
በሶሌ ዲገሉ ቀበሌ ከተገደሉ 12 ሰዎች መካከል አሥራ አንዱ የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆናቸውም ተገልጿል።
በኅዳር 17 ቀን 2016 ዓ.ም. በወረዳው በኮኘ ቀበሌ ታጣቂዎቹ በፈጸሙት ጥቃት የአንድ ቤተሰብ አባላት የነበሩ 8 ሰዎችን ገድለዋል የተባለ ሲሆን ጥቃት አድራሾች ሟቾችን ከቤት እያስወጡ አሰልፈው እንደገደሏቸው፣ የተወሰኑትም በቤታቸው ውስጥ እንደተገደሉ ለማወቅ ተችሏል ተብሏል።
ከሟቾች መካከል ጨቅላ ሕፃንን ጨምሮ ነፍሰጡር ሴቶች እና ከ80 ዓመት በላይ የሆናቸው አረጋዊ ይገኙበታል የተባለ ሲሆን ከተገደሉት ሰዎች በተጨማሪ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው በሕክምና ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ዞን፣ ጊዳሚ ወረዳ፣ በቤጊ-ጊዳሚ ሲኖዶስ ጊዳሚ ሰበካ ሥር የምትገኘው የመናኮ መናሞ ቀበሌ የሃሞ ቶኩማ አጥቢያ የመካነ ኢየሱስ ቤተ-ክርስቲያን አባላት የነበሩት 9 ምዕመናን፣ የቤተ-ክርስቲያኗ ሽማግሌዎች፣ የወጣቶች ኮሚቴ አባላት እንዲሁም ሌሎች አገልጋዮችን ኅዳር 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሌሊት 8፡00 ሰዓት አካባቢ እስካሁን ማንነታቸው ባልተለዩ በታጠቁ ቡድኖች ተገድለዋል።
የኢሰመኮ ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “በዚህ የግጭት ዐውድ እየደረሰ ያለው እጅግ አሠቃቂ ጉዳት ከዚህ የበለጠ ከመባባሱ እና የበለጠ ጉዳት ከመድረሱ በፊት መንግሥት ተገቢውን ሰላማዊና ፖለቲካዊ መፍትሔ ተግባራዊ እንዲያደርግ፣ ሁሉም ታጣቂ ቡድኖችና መንግሥት ሰብአዊ የተኩስ ማቆም አድርገው ወደ ውይይት እንዲያመሩ፣ መንግሥት በተለይ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰትና ለጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ አካባቢዎችና ነዋሪዎች በሙሉ የተሟላ ጥበቃና ደኅንነት እንዲያረጋግጥ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡