“በኮንሶ ከ10 በማይበልጡ ቀናት ውስጥ 66 ሰዎች ተገድለዋል”-ኢሰመኮ
ብዙ ቤቶችና ንብረቶች በእሳት መቃጠላቸውን እና ከመቶ ሺህ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውንም ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ይፋ አድርጓል
ደጋግመው ባገረሹት ግጭቶች ለ5 ያህል ጊዜያት የተፈናቀሉ እንዳሉም 39 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ያለው ኮሚሽኑ አስታውቋል
በደቡብ ክልል ኮንሶ ዞን ከኅዳር 1 እስከ ኅዳር 11 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ዳግም ባገረሹ ተከታታይ ግጭቶች 66 ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ በግጭቶቹ የደረሰው አሰቃቂ ግድያ፣ የአካል ጉዳት፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመት፤ የአካባቢው ሰብአዊ ቀውስ ዘላቂ እልባት ባለማግኘቱ እየተባባሰ መሄዱን የሚያሳይ መግለጫ አውጥቷል፡፡
መግለጫው ኮሚሽኑ ከኅዳር 12 ቀን እስከ ኅዳር 16 ቀን 2013 ዓ.ም በሀይበና እና በአይዴ ቀበሌዎች፣ በአርባምንጭ፣ በጊዶሌ እና በካራት ከተማዎች ተዘዋውሮ ባደረገው ምርመራ የደረሰበትን ግኝቶች ይፋ ያደረገበትን ፈጣን የዳሰሳ ሪፖርት ነው መሰረት አድርጎ የተሰጠ ነው፡፡
በሪፖርቱ ቢያንስ 66 ሰዎች ተገድለዋል ያለው ኮሚሽኑ 39 ሰዎች የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው እና ብዙ ቤቶችና ንብረቶች በእሳት እንደተቃጠሉ እንዲሁም ከመቶ ሺህ በላይ ነዋሪዎች እንደተፈናቀሉ ይፋ አድርጓል።
ደጋግመው ባገረሹት ግጭቶች እና የሰብአዊ መብት ቀውሶች የተፈናቀሉና የተጎዱትን ማቋቋም አፋጣኝ ትኩረትን እንደሚሻም ነው ያስታወቀው፡፡
ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) “አካባቢው ረዘም ላለ ጊዜ ሰላም አጥቶ የቆየበት ችግር ተገቢውን ትኩረት አላገኘም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ለ5ኛ ጊዜ የተፈናቀሉ ተጎጂዎች ጭምር መኖራቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ይህ “አሳዛኝ የሰብአዊ መብቶች ቀውስ” እንደሆነም ገልጸዋል።
ለተፈናቃዮች አስፈላጊውን ድጋፍ በአፋጣኝ ከማቅረብ ባሻገር፤ የፌዴራሉ እና የክልሉ መንግሥታት ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ ተቀናጅተው ዘላቂ ሰላም የሚያሰፍን መፍትሄ እንደሚገባ ነው ኮሚሽነሩ ያሳሰቡት።
የዞኑ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ከሰሞኑ ለሚዲያዎች በላከው ደብዳቤ በኮንሶ ዞን እና በአሌ ልዩ ወረዳ አጎራባች ቀበሌዎች ደጋግሞ ሲያጋጥም የነበረውን ግጭት ለማስቆም የሚያስችል የእርቅ ስነ ስርዓት ታህሳስ 13 ቀን 2013 ዓ/ም መካሄዱን አስታውቋል፡፡
ጽህፈት ቤቱ ከነገ በስቲያ እሁድ ታህሳስ 18 ቀን 2013 ዓ/ም የሁለቱ ህዝቦች የእርቀ ሰላም ኮንፈረንስ እንደሚካሄድም ነው ያስታወቀው፡፡