አሜሪካ በየመን የሀውቲ ታጣቂዎች ላይ አዲስ የአየር ጥቃት መፈጸሟ ተገለጸ
አሜሪካ ባለፈው ቅዳሜ በሀውቲ ታጣቂዎች ላይ መጠነሰፊ የአየር ጥቃት የጀመረችው በቀይ ባህር በሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቆም ነው

በጥቃቱ ቢያንስ 53 ሰዎች መገደላቸውን በሀውቲ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አኔስ አልስባሂ ትናንት ተናግረዋል
አሜሪካ በየመን የሀውቲ ታጣቂዎች ላይ አዲስ የአየር ጥቃት መፈጸሟ ተገለጸ።
አሜሪካ በዛሬው እለት በየመን የሀውቲ ታጣቂዎች ላይ አዲስ የአየር ጥቃት በመፈጸም ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ጥር ወር ስልጣን ከያዙ ወዲህ በመካከላቸው ምስራቅ እያካሄደች ያለውን ትልቅ ዘመቻ አድማስ አስፋታለች።
አሜሪካ ባለፈው ቅዳሜ በኢራን በሚደገፉት የሀውቲ ታጣቂዎች ላይ መጠነሰፊ የአየር ጥቃት የጀመረችው በቀይ ባህር በሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቆም ነው።
የሀውቲዎችን አል ማሲራህ ቴሌቪዥን ጠቅሶ ሮይተርስ እንዘገበው አሜሪካ በዛሬው እለት በፈጸመችው ጥቃት ከዋና ከተማዋ ሰንዓ ሰሜን በኩል የሚገኙት ሁለት የቀይ ባህር ከተሞች ሆዴይዳህና አል ጃውፍ ኢላማ ተደርገዋል።
በጥቃቱ ቢያንስ 53 ሰዎች መገደላቸውን በሀውቲ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አኔስ አልስባሂ ትናንት ተናግረዋል።
አልስባሂ በጥቃቱ ከተገደሉት ውስጥ አምስቱ ህጻናት ሁለቱ ሴቶች መሆናቸውን እና ሌሎች 98 ደግሞ መቁሰላቸውን በኤክስ ገጹ ገልጿል።
አብዛኛውን የየመን ክፍል የተቆጣጠሩት የሀውቲ ታጣቂዎች ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ ለሚገኘው የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ አጋርነት ለማሳየት በሚል ነበር ከህዳር 2023 ጀምሮ ከአሜሪካ፣ እስራኤልና ዩናይትድ ኪንግደም(ዩኬ) ጋር ግንኙነት እንዳላቸው በሚጠረጥሯቸው በቀይ ባህር በሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ ጥቃት ማድረስ የጀመሩት። ሮይተርስ የአሜሪካ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው አሜሪካ ኢራን ወደ ኑክሌር ድርድር እንድትመጣ በማዕቀብ ጫና እየፈጠረች ባለበት ወቅት የምትፈጽመው ይህ ጥቃት ለሳምንታት ሊቀጥል ይችላል።
የሀውቲ መሪ አብዱል ማሊክ አል-ሀውቲ አሜሪካ የመንን ማጥቃቷን እስከቀጠለች ድረስ ቡድኑ በቀይ ባህር የሚንቀሳቀሱ የአሜሪካ መርከቦችን ማጥቃቱን እንደሚቀጥል ገልጿል።
"ወረራቸውን የሚቀጥሉ ከሆነ እኛም ትንኮሳችንን እንቀጥላለን "ብሏል መሪው።
የሀውቲ የፖለቲካ ቢሮ የአሜሪን ጥቃት የጦር ወንጀል ሲል ገልጾታል። ሩሲያ አሜሪካ ጥቃቱን እንድታቆም አሳስባለች።
የሀውቲ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ሰኞ ጠዋት ባወጣው መግለጫ ቡድኑ ዩኤስኤስ ሀሪ ኤስ.ቱርማን የተባለችውን የአሜሪካ የጦር ጄት ተሸካሚ መርከብ ቀይ ባህር ላይ ኢላማ አድርጌያለሁ ብሏል።
እስራኤል በ2023 ሀማስ ያደረሰባትን ጥቃት ተከትሎ ባካሄደችው ጦርነት የኢራን አጋር የሆኑትን ታጣቂ ቡድኖች የሀማስ እና ሄዝቦላን መሪዎቻቸውን በመግደል ጭምር እንዲዳከሙ አድርጋለች።
ቡድኑ ባለፈው ሳምንት እስራኤል ወደ ጋዛ እርዳታ እንዳይገባ የጣለችውን እገዳ የማታነሳ ከሆነ በቀይ ባህር በሚያልፉ የእስራኤል መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸም እንደሚጀምር ገልጾ ነበር።
ፕሬዝደንት ትራምፕ የሀውቲ ታጣቂዎች ዋና ደጋፊ ነች የምትባለውን ኢራንን ድጋፍ ማድረጓን እንድታቆም፣ የማታቆም ከሆነ ግን "አሜሪካ ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ እንደምታደርጋት" ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።