ትራምፕ በዩክሬን ጦርነት ማቆም ዙሪያ ከሩስያው አቻቻው ቭላድሚር ፑቲን ጋር እንደሚወያዩ ተናገሩ
ሁለቱ መሪዎች አሜሪካ ባቀረበችው የ30 ቀናት ተኩስ አቁም ዙሪያ እንደሚመክሩ ተገልጿል

የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈረመ አውሮፓ እና ብሪታንያ የሰላም አስከባሪ ጦር ለመላክ እየተዘጋጁ ነው
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም እየተደረገ በሚገኘው ጥረት ዙሪያ ከሩስያው አቻቻው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በነገው ዕለት እንደሚወያዩ ተናግረዋል፡፡
ሁለቱ መሪዎች ለውይይት ቀጠሮ የያዙት ወደ ሩስያ ያቀኑት የአሜሪካ ልዑካን ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸው ከተገለጸ በኋላ ነው፡፡
ትራምፕ ለጋዜጠኞች ባደረጉት ንግግር “ጦርነቱን ለማስቆም እየሞከርን ነው ሊሳካም ላይሳከም ይችላል፤ ነገር ገን የሚሳካበት ሰፊ እድል እንዳለ ይታየኛል” ብለዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት በዩክሬን ተቀባይነት ያገኘውን የ30 ቀናት የተኩስ አቁም በፑቲን ዘንድ ድጋፍ እንዲኖረው ፕሬዝዳንቱ እሞከሩ ይገኛሉ፡፡
ፑቲን በበኩላቸው በስምምነቱ ነጥቦች ላይ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ እና ለጦርነቱ መጀመር ዋነኛ መንስኤ የሆኑ የሞስኮ የደህንነት ጥያቄዎች በጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ውስጥ እንዲካተት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ከዚህ ባለፈ ዩክሬን በዘላቂነት የኔቶ አባል ሀገር እንደማትሆን እና ወታደራዊ ድርጅቱ ወደ ሩስያ ድንበሮች የሚያደርገውን መስፋፋት እንደሚያቆም የደህንንት ዋስትና እንዲሰጣትም ጠይቃለች፡፡
በሞስኮ ጉብኝት ያደረጉት የትራምፕ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ስቲቭ ዊትኮቭ ሩስያ የምትስማማበት እድል እንዳለ ገልጸው ከዛ በፊት ማለቅ ያለባቸው በርካታ ስራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
አማካሪው ከኤቢሲ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ ሩስያ በተኩስ አቁሙ ለመስማማት በምስራቃዊ ዩክሬን የተቆጣጠረቻቸውን ግዛቶች ይዛ ለመቀጠል ቅድመ ሁኔታ አስቀምጣ እንደሆነ ተጠይቀው ነበር፡፡
በምላሻቸውም “ሰላምን ማስፈን እና የሶስት አመቱን ጦርነት ለማስቆም ቁርጠኛ ከሆንን መሬት ላይ ያሉ እውነታዎችን ለመቀበል ዝግጁ መሆን አለብን” ሲሉ ድፍን ያለ መልስ ሰጥተዋል፡፡
በሌላ ቃለ ምልልስ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩብዮ የድርድር ሂደቱ ጠንካራ ስራ እንደሚጠይቅ ገልጸው ሁለቱም ወገኖች የሚያነሷቸውን ልዩነቶች ለማጥበብ በቅድሚያ ተኩስ ማቆም ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
ጦርነቱ በቅርቡ ሊቆም እንደሚችል እምነት እንዳላቸው የተናገሩት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮለድሚር ዘለንስኪ በበኩላቸው የዩክሬን ሉዐላዊነት ለድርድር እንደማይቀርብ እና ሞስኮ በጦርነቱ እና ከጦርነቱ በፊት ከተቆጣጠረቻቸው የዩክሬን ግዛቶች መልቀቅ እንደሚኖርባት አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ብሪታንያ እና አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት ሞስኮ እና ኪየቭ የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ስምምነቱ አለመጣሱን ለማረጋገጥ የሰላም አስከባሪ ሀይል ወደ ስፍራው ለመላክ እየተዘጋጁ ነው፡፡
በእነዚህ ሁሉ ልዩነቶች መካከል ትራምፕ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ቅድሚያ ከሰጧቸው አጀንዳዎች መካከል ዋነኛ ጉዳይ የሆነውን የዩክሬን ጦርነት ማስቆም እውን ለማድረግ ከፑቲን ጋር በነገው ዕለት የሚያደርጉት ውይይት ተጠባቂ ነው