ሕብረተሰቡ ከአደረጃጀት ጋር በተያያዘ የተለያዩ ሀሳቦችን አንስተዋል
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ አደም ፋራህ ዛሬ ከሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ከራያ ሕዝብ ጋር መወያየታቸውን የውይይቱ ተሳታፊዎች ለአል ዐይን ኒውስ አስታወቁ፡፡
ከአቶ አደም ፋራህ ጋር የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ ገዱ አንዳርጋቸው፣ በብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሲቪክ ማህበራት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር አለሙ ስሜ (ዶ/ር)፣ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሚሊዮን ማቴዎስ እና የብልፅግና ፓርቲ አመራር ሞገስ ባልቻ ተካተዋል፡፡ ልዑኩ በአላማጣ ከተማ ተገኝቶ የነዋሪዎችን ፍላጎት ለመረዳት የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል፡፡
በአላማጣ በተካሄደው የሕዝብ ውይይት በርካታ የራያ አላማጣ ነዋሪዎች መሳተፋቸው የተገለጸ ሲሆን ከሕብረተሰቡ የአደረጃጀት እና ሌሎች ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ የተለያዩ ሀሳቦች መነሳታቸውን የውይይቱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡ በትግራይ ክልል የመቀጠል ፣ ወደ አማራ ክልል የመጠቃለል እንዲሁም በልዩ ዞን ደረጃ ራስን ችሎ የመደራጀት ሀሳቦች መነሳታቸውን ሰምተናል፡፡