“ከእናትና አባትህ የማትጠብቀው አይነት ክህደት በሰራዊቱ ላይ ተፈጽሟል” የሰ/ዕዝ ም/ኦፐሬሽን አዛዥ
ወደፊት ዝርዝር ታሪኩን በጽሁፍ በሰፊው እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል
መከላከያ ሰራዊት በቅርቡ ከእገታ ካስለቀቃቸው የአመራር አባላቱ አንዱ የሆኑት ብ/ጄኔራል አዳምነህ መንግስቴ መግለጫ ሰጥተዋል
ከእገታ ከተለቀቁ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ብ/ጄነራል አዳምነህ ፣ የሕወሓት አመራሮች በቅርበት ይከታተሏቸው እንደነበር ገልጸው የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሕወሓት አመራችን ነጥሎ ጠባብ መንገድ ላይ ባደረገው የአየር ድብደባ ተሸከርካሪዎቻቸውን ማቃጠሉን አስታውቀዋል፡፡ የሕወሓት አመራሮችም ወደኋላ ሲመለሱ ተሸከርካሪዎቻቸውን በመምታት መንገዱ እንዲዘጋባቸው ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አመራሮቹ መሄጃ በማጣታቸው የነበራቸውን ተሽከረካሪዎች እና ንብረት እየጣሉና እያንጠባጠቡ ሲበታተኑ መከላከያ ሰራዊት ደርሶ አብረዋቸው የነበሩትን ሁሉ ነጻ ማውጣቱን ገልጸዋል፡፡
መከላከያ ሰራዊት በሕወሓት ታጣቂዎች የታፈኑትን የሰራዊት አመራርና አባላትን ነጻ ሲያወጣ ጠላትና ወገንን የለየ አስደናቂ ኦፐሬሽን እንዳከናወነ ብ/ጄኔራል አዳምነህ ገልጸዋል፡፡ “መከላከያ ሰራዊት አባላትን በማይጎዳ መልኩ ጥንቃቄ የተሞላበት እርምጃ ወስዷል” ብለዋል።
በአፈናው ወቅት ስለነበረው ሁኔታ ሲያስረዱ “ስሜቱን መግለጽ ያጥረኛል ፤ እናትና አባትህ ይክዱኛል ብለህ የማትጠብቀው አይነት ክህደት ተፈጽሟል ፤ ቤታችን ነው ፤ ሰላም ነው፤ ባልንበት ቦታ በተደራጀ ኃይል አፈና ተካሂዶብናል” ብለዋል፡፡
የአፈናው ጊዜ በሙሉ በርካታ ውጣ ውረዶች እንደነበሩት የገለጹት አዛዡ ፣ ረጅም የእግር ጉዞዎች በቀንም በሌሊትም ያለዕረፍት ሲጓዙ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ህይወታቸውን ካተረፉላቸው የመከላከያ ሰራዊት አባላት ጋር በመሆን ወደፊት ዝርዝር ታሪኩን በጽሁፍ በሰፊው እንደሚያቀርቡም ብርጋዴር ጄኔራል አዳምነህ መንግስቴ ገልጸዋል፡፡
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ላይ በሕወሓት ታጣቂዎች ጥቃት ተፈጽሞባቸው የታፈኑት የሰሜን እዝ መከላከያ ሰራዊት አመራሮች ሽሬ ከተማ ሲደርሱ በሰራዊቱ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን በርካታ የሰራዊቱ አባላት ታፍነው የሰነበቱ አመራሮቻቸውንና ጓደኞቻቸውን ሲያገኙ ወደሰማይ በመተኮስ ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡
ህዳር 30 ቀን ከሰዓት በኋላ የሕወሓት ቡድን አጋቾች አዴት በተባለ አካባቢ በእግር ሲያጓጉዟቸው የነበሩትን ከ1ሺህ በላይ የሰራዊቱን መኮንኖች በመልቀቅ በየአቅጣጫው መበታተኑ ተገልጿል፡፡ ታፍነው የሰነበቱ የሰራዊቱ አመራሮች መንግስት ላደረገው የህይወት አድን ጥረት ምስጋና አቅርበዋል ሲል ኢፕድ ዘግቧል።