የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የፓሪስ ኦሎምፒክ መክፈቻ “አስነዋሪ” ነበር አለች
የቤተክርስቲያኗ ቋሚ ሲኖዶስ ባወጣው መግለጫ በመክፈቻው “ክብረ ነክና ሊወገዝ የሚገባው ሰይጣናዊ ድርጊት” ታይቷል ብሏል
የፓሪስ ኦሎምፒክ አዘጋጆች በመክፈቻው ለታየውና ክርስቲያኖችን ላስቆጣው ትዕይንት ይቅርታ መጠየቃቸው ይታወሳል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የፓሪስ ኦሎምፒክ መክፈቻ “አስነዋሪ” ነበር አለች ።
የቤተክርስቲያኗ ቋሚ ሲኖዶስ ባለፈው አርብ በተካሄደው የኦሎምፒክ መክፈቻ ዙሪያ መግለጫ አውጥቷል።
የዓለም ኦሎምፒክ ስፓርታዊ ውድድር መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ የተካሄደውን አስነዋሪ ትዕይንት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
መግለጫው በኦሎምፒክ መክፈቻ ስነስርአቱ “በመላው ክርስቲያኖች ዘንድ ከፍተኛ ክብር የሚሠጠውን ምስጢረ ቁርባንን ያቀለለ፣ የተመሳስይ ጾታ ጋብቻን፣ የግብረ ሰዶማውያንን እኩይ ተግባር በወገንተኛነት የደገፈ ትርኢት” ታይቷል ብሏል።
በኦሎምፒክ መክፈቻው “የሃይማኖትን ነጻነት የሚጋፉ፣ ጾታ የሚለውጡ ሰዎችን የሚያበረታቱ” ትይንቶች መቅረባቸውን በመጥቀስም፥ አጠቃላይ መክፈቻው በክርስትና ሃይማኖትና በክርስቲያኖች ላይ የተፈጸመ ቀጥተኛ ጥቃት ነው ሲልም ገልጿል።
ድርጊቱ የሌሎችን የእምነት የባህልና የማህበራዊ ዕሴት ማክበር ልዩ ቦታ በሚሰጠው የኦሎምፒክ ስፖርታዊ ጨዋነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥር መሆኑንም ነው መግለጫው የጠቆመው።
በፓሪሱ ኦሎምፒክ መክፈቻ የታዩ “ከሰለጠነው አለም የማይጠበቁ” ትዕይንቶች በቅዱሳት መጽሃፍትም ሆነ በሰው ልጅ ሰብአዊ አኗኗር ፈጽሞ ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑንም አብራርቷል።
ቋሚ ሲኖዶሱ በመግለጫው አንዱ የሌላውን የእምነትና የአምልኮ ነጻነት ማክበር በሃይማኖት ቀኖናት ብቻ ሳይሆን በአለም ሀገራት የሰብአዊ መብትና የእምነት ሕግጋት የተደነገገ መሆኑን አውስቷል።
ይሁን እንጂ በፓሪስ አሎምፒክ በየአራት አመቱ ከሚካሄደው ውድድር ጋር በማይገናኝ ሁኔታ “አስነዋሪ ተግባር ተፈጽሟል” መፈጸሙን በማከል።
ተግባሩ “ሃይማኖታችንን የሚጋፋ፣ መንፈሳዊ እሴቶቻችንን የሚያጠፋ ክብረ ነክና ሊወገዝ የሚገባው ሰይጣናዊ ድርጊት” ነው በሚልም የቤተክርስቲያኗ ቋሚ ሲኖዶስ በጽኑ እንዳወገዘው አመላክቷል።
የዓለም አቀፍ የኦሎምፒክ ኮሚቴና ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላትም በክርስቲያኖች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ የቀሰቀሰውን ድርጊት በግልጽ እንዲቃወሙ ነው ጥሪውን ያቀረበው።
የፓሪስ ኦሎምፒክ መክፈቻ ላይ የታዩ ጉዳዮች አሁንም ድረስ ተቃውሞ ማስነሳታቸውን ቀጥለዋል።
የሊዮናርዶ ዳቬንቺን የኢየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻው እራት ስዕልን በመጠቀም የተላለፈውመልዕክት ክርስቲያኖችን አስቆጥቷል።
የፈረንሳይ፣ የግሪክ፣ የሩሲያ እና የግብጽ ታላላቅ የክርስትና እምነት መሪዎች ድርጊቱ መላው ክርስቲያንን ባልተገባ መንገድ የገለጸና ለሀይማኖቱም ተገቢውን ክብር ያልሰጠ አሳፋሪ ድርጊት ነው ሲሉ አውግዘውታል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም አዘጋጅ ኮሚቴው በጉዳዩ ላይ ማስተካከያ እንዲያደርግ እና ይቅርታ እንዲጠይቅ በርካቶች ግፊት ሲያደርጉ እንደነበር ይታወሳል፡፡
አዘጋጆቹ የቀረበባቸውን ትችት “የነጻነት ሀገር መሆናችንን የሚያሳይ መልዕክት ያስተላለፍንበት ነው” በማለት ለማስተባበል ቢሞክሩም የተቃውሞዎች መበረከትን ተከትሎ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡