ስሟ በስህተት መጠራቱ ያበሳጫት ደቡብ ኮሪያ ከዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ጋር አስቸኳይ ስብሰባ እንዲደረግ ጠይቃለች
በፓሪስ ኦሎምፒክ መክፈቻ ላይ የታዩ ዋና ዋና ስህተቶች ምን ምን ናቸው?
በየአራት ዓመቱ የሚካሄደው ተወዳጁ የኦሎምፒክ ውድድር ከ100 ዓመት በኋላ ወደ ፓሪስ ተመልሷል፡፡
ትናንት አመሻሽ የተጀመረው ይህ ውድድር የመክፈቻ ፕሮግራሙን ከ208 ሀገራት የተውጣጡ ከ7 ሺህ 500 በላይ የዓለም አትሌቶችን ጨምሮ ሚሊዮኖች ታድመውታል፡፡
ይሁንና የውድድሩ ተሳታፊ ሀገራት በሴን ወንዝ ላይ ሲያልፉ መድረክ መሪዎች ሀገራትን አሳስተው ጠርተዋል።
በእንግሊዝኛ እና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎች ደቡብ ኮሪያን እንደሰሜን ኮሪያ መጥራታቸው ቁጣን ቀስቅሷል።
ክስተቱ የተፈጠረው የደቡብ ኮሪያ አትሌቶች ሰንደቅ አላማቸውን ይዘው እያለፉ እና እያውለበለቡ እያለ በስህተት ሰሜን ኮሪያ ተብለው ተጠርተዋል።
ደቡብ ኮሪያዊያን በስህተት መጠራታቸው እንዳበሳጫቸው በመንግስታቸው በኩል እና በማህበራዊ ትስስር ገጾች ተናግረዋል።
በፓሪስ ኦሎምፒክ ላይ በ142 አትሌቶች በ21 ውድድሮች ላይ የምትሳተፈው ደቡብ ኮሪያ አወዳዳሪው የኦሎምፒክ ኮሚቴ ጋር አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ ጠይቃለች።
በስፍራው ያሉት የደቡብ ኮሪያ ምክትል ስፖርት እና ባህል ሚንስትር ጃንግ ሚራን እንዳሉት የተፈጸመው ስህተት እንዳበሳጫቸው ገልጸው ዳግም ስህተት እንዳይፈጠር አስጠንቅቀዋል።
ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ በበኩሉ ለተፈጠረው ስህተት በኮሪያ ቋንቋ ይቅርታ ጠይቆ ስህተት እንደማይደገም አስታውቋል።
በለንደን እና ቶኪዮ ኦሎምፒክ ውድድሮች ላይ ያልተሳተፈችው ሰሜን ኮሪያ በፓሪስ ኦሎምፒክ ላይ በ16 አትሌቶች ትሳተፋለች።
ሌላኛው አነጋጋሪ የሆነው በውድድሩ መክፈቻ ላይ በሊኦናርዶ ዳቬንቺ የተሳለው በክርስትና ዕምነት ዘንድ "የመጨረሻው እራት" በሚል የሚታወቀውን ስዕል በመክፈቻው ላይ መቅረቡ ነው።
በርካታ የክርስትና ዕምነት ተከታዮች ስዕሉ የቀረበበት መንገድ ስፖርት ከሀይማኖት ነጻነት አንጻር ስህተት መሆኑን በመናገር ላይ ናቸው።
በትናንትናው ዕለት ፓሪስን ከቀሪ ሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች ጋር የሚያገናኙ ፈጣን ባቡር መስመር ላይ የተፈጸመው ጥቃት በዓሉ ታዳሚዎች ላይ እክል ፈጥሯል ተብሏል።
በባቡር መሰረተ ልማቱ ላይ ለደረሰው ጥቃት እስካሁን ሀላፊነት የወሰደ አካል የሌለ ሲሆን ትራንስፖርቱ አሁንም እንደተቋረጠ እና መንግስትም እስካሁን ተጠርጣሪዎቹን አላሳወቀም።