ፓትርያርኩ በአዲሱ ዓመት የመሳሪያ አፈሙዞች በሙሉ ወደ መጋዝን መግባት እንዳለባቸው አሳሰቡ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የ2016 ዓመተ ምሕረት የዘመን መለወጫን በማስመልከት ከሰሜን አሜሪካ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል
ኢትዮጵያውያን ከጠብና ጦርነት ርቀው በቀደመ ባህልና ትውፊታቸው በመታገዝ ፍቅራቸውን እንዲያድሱም ጥሪ አቅርበዋል
በአዲሱ ዓመት የሰው ሕይወትን የሚቀጥፉ የመሳሪያ አፈሙዞች በሙሉ ወደ መጋዝን መግባት አለባቸው አሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ።
ፓትርያርኩ የ2016 አዲስ አመትን አስመልክተው ከሰሜን አሜሪካ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያውያን በአዲሱ አመት ከጠብ እና ጦርነት ርቀው በቀደመ ባህልና ትውፊታቸው በመታገዝ ፍቅራቸውን እንዲያድሱ አሳስበዋል።
ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም ነው የጠየቁት።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በመልዕክታቸው በአንድ ምድር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም በወሰን እና መሰል ጉዳዮች ቅራኔ እና ግጭት ውስጥ መግባታቸውን በመተው በአንድነታቸው ላይ እንዲያተኩሩ አሳስበዋል።
ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ተፎካካሪዎች፣ ልሂቃን፣ የስቪክ ማኅበራትና ምሁራን በኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት ብቻ እንዲያደርጉ በመጠየቅም ካለፈው ስህተታችን እንማር የሚል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ኢትዮጵያን እየጎዱ ናቸው ያሏቸውን የመለያየት፣ ፉክክር፣ ንቀት፣ የራስን ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ መጣር እና ጊዜ አገኘሁ ብሎ ኃይልን መጠቀምን የመሰሉ አስተሳሰቦች እና ድርጊቶች ከአሮጌው ዓመት ጋራ አብረው መወገድ እንዳለባቸውም ነው ያነሱት።
በአዲሱ ዓመት የመሳሪያ አፈሙዞች በሙሉ ወደ መጋዝን ገብተው ችግሮችን በውይይት፣ አልያም በሕግ እየተፈቱ የሀገርና የሕዝብ ሉዓላዊነት ነጻነትና አንድነት ማረጋገጥ እንደሚገባም በማከል።
“ሀገርንና ሕዝብን ለዘለቄታው በአንድነት የሚያስቀጥሉ የሕግ የበላይነትን ማክበር፣ እኩልነትን ማረጋገጥ፣ የጋራ ተጠቃሚነትን እውን ማድረግ፣ የተጐዳውን መደገፍ፣ ሆድ የባሰውን ማለዘብ፣ የተጠቃውን ማጽናናት” ይገባልም ነው ያሉት።
“ኢትዮጵያውያን የሆናችሁ ልጆቻችን ሁሉ ይህንን ጥሪያችንን ተቀብላችሁ የጥፋት መሳሪያችሁንም አስቀምጣችሁ ወደ ሰላም ማእድ ቀርባችሁ በወንድማማችነት መንፈስ ችግራችሁን በክብ ጠረጴዛ በውይይት በመፍታት የሀገሪቱንና የሕዝቡን አንድነት እንድታስቀጥሉ ሁሉን በሚያይ እግዚአብሔር ስም እንማጸናችኋለን” ሲሉም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አዲሱ አመት 2016 “ሆድ የባሰው የሚጽናናበት፣ ፍትሕና ርትዕ የሚሰፍንበት፣ የመሳሪያ ድምፅ የማይሰማበት፣ ፍጹም የተግባቦት ዓመት” እንዲሆንም ተመኝተዋል።