“ጥቅምት 24 የተጨፈጨፈው ሰራዊቱ ብቻ አይደለም የኢትዮጵያ ህዝብም ጭምር ነው”- ጠ/ሚ ዐቢይ
ህወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት የፈፀመበት 1ኛ ዓመት በመላ ሀገሪቱ እየታሰበ ነው
እለቱ “ኢትዮጵያ በእኛ መሥዋዕትነት የምትቀጥል ሀገር መሆኗን ዳግም ቃል ኪዳን የምንገባበት ነው” ብለዋል
ህወሓት ጥቅምት 24 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ጥቃት 1ኛ ዓመት መታሰቢያ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው።
በመከላከያ ሚኒስቴር ቅጥር ግቢ በተካሄደ በመርሃ ግብር ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ የመከላከያ ሚኒስትር ዶ/ር አብረሃም በላይ፣ የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ፣ ምክትል ኢታማዦር ሹም ጀነራል አበባው ታደሰ እና የሠራዊት አባላት ተገኝተዋል።
መርሃ ግብሩም ጥቃት ለደረሰባቸው የሰራዊት አባላት የህሊና ጸሎትና የሻማ ማብራት ስነስርዓት ተካሂዶል።
በመታሰቢያ መርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባደረጉት ንግግር “ጥቅምት 24 2013 ዓ.ም በግፍ የተገደለው ወታደር ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያም ተገድላለች” ብለዋል።
“በእለቱ የተጨፈጨፈው ሰራዊቱ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብም ጭምር ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በንግግራው አክለውም “ጠላትን በደማችን እና በአጥንታችን ቀብረን ኢትዮጵያን ዳግም ቀና እናደርጋለን ሲሉም ተናግረዋል።
“እኔም ወታደር ነኝ የምንል የኢትዮጵያ ልጆች ኢትዮጵያን ለመበተን የተነሱትን ኃይሎች በጀ የማንል መሆናችንን፣ አንድ መሆናችንን፣ በእኛ መሥዋዕትነት የምትቀጥል ሀገር መሆኗን ዳግም ቃል ኪዳን የምንገባበት ዕለት ነው”ም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ነፃ እስክትሆን እያንዳንዱ ዜጋ “እኔም የኢትዮጵያ ወታደር ነኝ’’ ብሎ ያለውን ስንቅ እና ትጥቅ ለመከላከያ እንዲያቀርብ እንዲሁም ለውትድርና አቅሙ የደረሰ ወጣት በራሱ ፈቃድ መከላከያን ተቀላቅሎ እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
በፌደራል ምንግስት የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል አለመግባባት የተፈጠረው፤ ኢትዮጵያን ለ27 አመታት ሲያስተዳድር የነበረውየገዥ ፓርቲ ግባሮች በመዋሃድ ብልጽግና ፓርቲን ሲመሰርቱ ህወሓት የውህደቱ አካል አልሆንም ብሎ በማፈንገጡ ነው።
ህወሓት የፌደራል መንግስቱ ህገወጥ ነው ያለውን ምርጫ ማካሄዱም የአልመግባባቱ ጡዘት ውጤት ነበር።
በሁለቱ አካላት መካከል የነበረው አለመግባባት ወደ ወታራዊ ግጭት ያመራው፤ ጥቅምት 24፣2013 ህወሓት በትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ነበር፡፡
ክህደት ፈጽሟል ባለው ህወሓት ላይ የህግ ማስከበር ዘመቻ በማወጅ የትግራይ ዋና ከተማና ብዙ ቦታዎችን መያዝ የቻለው መንግስት ከ8 ወራት በኋላ ለትግራይ ህዝብ የጽሞና ግዜ ለመስጠት በማሰብ ከትግራይ ክልል ሰራዊቱን ማስወጣቱ ይታወሳል።
መንግስት ጦሩን ከክልሉ ማስወጣቱን ተከትሎ፣ ሕወሓት ወደ አማራ አፋር ክልል በመግባት ጥቃት በመሰንዘር፤ ሰዎች እንዲገደሉና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲፈናቀሉ ማድረጉን መንግስት ገልጿል።
መንግስት በኢትዮጵያ ሉአላዊነት ላይ ተደቅኗል ያለውን አደጋ ለመቀልበስ በትናንትናው እለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል።