በግጭቱ ወቅት ክብራቸውና ስብእናቸው የተገፈፈባቸውን ሰዎች ምስክርነት መስማት “ልብ ሰባሪ ነው”- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ
የኢትዮጵያ መንግስት፣ የምርመራ ቡዱኑ ይፋ ባደረገው ሪፖርት የተወሰኑ ይዘቶች ላይ ትልቅ ቅሬታ እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) የሰብአዊ መብት ቢሮ በትግራይ ግጭት ዙሪያ በጋራ ያደረጉት የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርምራ ውጤር በዛሬው እለት ይፋ አድርገዋል፡፡
በሪፖርቱ ላይ መንግስት የማይቀበላቸው ጉዳዮች መኖራቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግስት ተጎጅዎችን ለመርዳት፣ ተጠያቂነትን ለማስፈንና ጥቃትን ለመከላከል ስለሚጠቅመን ሪፖርቱን እንደ ጠቃሚ ሰነድ እንደሚቀበለው ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚስኒትር ዐብይ ሪፖርቱ ግጭቱ ከተጀመረ በኃላ ንጹሃን ኢትዮጵያውን ላይ የደረሰውን አሰቃቂ ጥቃት ሰንዷል፤በግጭቱ ወቅት ክብራቸውና ስብእናቸው የተገፈፈባቸውን ሰዎች ምስክርነት መስማት “ልብ ሰባሪ ነው”ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ምንም እንኳን መንግስት ለጥምር የምርመራ ቡድኑ ስጋቱን ቢያሳውቅም፤ ሪፖርቱ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የተሰነዘሩ አሳሳችና መሰረተቢስ ክሶችን አለማካተቱ መንግስትን እንዳስደሰተው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት “ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያነት ይጠቀማል”፣ “የዘርማጥፋት ፈጽሟል፤ለንጹሃን ሰብአዊ እርዳታ እንዳይደርስ አድርጓል” የሚል ክስ ሲቀርብበት ቆይቷል፡፡ በሪፖርቱ መንግስት ፈጠራ ናቸው ያላውች እነዚህ ክሶች አልተካተቱም፡፡
በሪፖርቱ በግጭቱ ተሳትፈው የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽመዋል ያላቸው አካላትም፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት፣ የትግራይ ልዩ ሀይል እና ሚሊሻ እንዲሁም የአማራ ልዩ ሀይል እና ሚሰሻዎች መሆናቸውንም አመላክቷል
ሪፖርቱ ከጥቅምት 24 2013 ዓ.ም እስከ ሰኔ 21 2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ንጹሃንና ማጥቃት፣ የንጹሃንን ንብረት ማጥቃት፣ ከህግ ውጭ የሆነ ግድያ፣ ማሰቃየት እና ማገት፣ ህገ ወጥ የሆነ እስር፣ ጾታዊ እና ሌሎችም የሰብዓዊ መብት ጥሰጥ ጥቃቶች መፈጸማቻን ጠቅሷል።
በፌደራል ምንግስት የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል አለመግባባት የተፈጠረው፤ ኢትዮጵያን ለ27 አመታት ሲያስተዳድር የነበረውየገዥ ፓርቲ ግባሮች በመዋሃድ ብልጽግና ፓርቲን ሲመሰርቱ ህወሓት የውህደቱ አካል አልሆንም ብሎ በማፈንገጡ ነው።
ህወሓት የፌደራል መንግስቱ ህገወጥ ነው ያለውን ምርጫ ማካሄዱም የአልመግባባቱ ጡዘት ውጤት ነበር።
በሁለቱ አካላት መካከል የነበረው አለመግባባት ወደ ወታራዊ ግጭት ያመራው፤ ጥቅምት 24፣2013 ህወሓት በትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ነበር፡፡
ክህደት ፈጽሟል ባለው ህወሓት ላይ የህግ ማስከበር ዘመቻ በማወጅ የትግራይ ዋና ከተማና ብዙ ቦታዎችን መያዝ የቻለው መንግስት ከ8 ወራት በኋላ ለትግራይ ህዝብ የጽሞና ግዜ ለመስጠት በማሰብ ከትግራይ ክልል ሰራዊቱን ማስወጣቱ ይታወሳል።
መንግስት ጦሩን ከክልሉ ማስወጣቱን ተከትሎ፣ ሕወሓት ወደ አማራ አፋር ክልል በመግባት ጥቃት በመሰንዘር፤ ሰዎች እንዲገደሉና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲፈናቀሉ ማድረጉን መንግስት ገልጿል።መንግስት በኢትዮጵያ ሉአላዊነት ላይ ተደቅኗል ያለውን አደጋ ለመቀልበስ በትናንትናው እለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል።