መከላከያው አድዋንና የአዲግራትን ዙሪያ መቆጣጠሩንም አስታውቋል
መከላከያው አክሱምን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሯል ተባለ
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ ዛሬ ኅዳር 11 2013 መከላከያ ሠራዊቱ አክሱምን አድዋንና የአዲግራትን ዙሪያ መቆጣጠሩን አስታወቀ።
በምዕራብ ግንባር እያጠቃ ያለው ሰራዊቱ ከሽሬ በኋላ ሰለህለሃ ላይ የመሸገ የሕወሐት ኃይል ገጥሞት ነበር ያለው መረጃ ማጣሪያው በስፍራው የመሸገው ኃይል መንገዱን በዶዘር ቆርጦና አስፓልቱን አበላሽቶ በቦታው ከባድ መከላከል ማድረጉን ገልጿል።
ሆኖም ሠራዊቱ ተከላካይ ኃይሉን ሠብሮ በመግባት አክሱምን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሯል እንደ መረጃ ማጣሪያ ድረገጹ መግለጫ።
ተከላካይ ኃይሉ ከአክሱም ወደ አድዋ በነበረው ጉዞ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ለመከላከል ቢሞክርም፣ በመከላከያ ሠራዊቱ ድል ሆኗልም ብሏል፡፡
እንደ መግለጫው ከሆነ መከላከያው እንቲጮንና የአዲግራትን ዙሪያ ተቆጣጥሮ ወደ አዲግራት ከተማ እየገሠገሠ ይገኛል፡፡
አያሌ የህወሓት ተዋጊዎች እጅ ሰጥተዋል ብሏል መግለጫው፡፡
እጅ ከሰጡት መካከል ሰራዊቱን ከድተው ሲዋጉ የነበሩ ወታደሮች እንደሚገኙበትም ታውቋል።