“አክሱምን የተመለከተው የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መግለጫ ጭፍጨፋውን ለመሸፋፈን ያለመ ነው”-አምነስቲ ኢንተርናሽናል
በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ መግለጫ በሁለት ጉዳዮች ላይ ልዩነቶች እንዳሉትም ነው ያስታወቀው
አምነስቲ ጭፍጨፋውን በዓለም አቀፍ ገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጠይቋል
የሰሞኑን የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መግለጫ በአክሱም የተካሄደውን ጭፍጨፋ ለመሸፋፈን ያለመ እንደሆነ አምነስቲ ኢንትርናሽናል ገለፀ፡፡
አምነስቲ ባወጣው መግለጫ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ በሁለት ጉዳዮች ላይ ልዩነት እንዳለው አስታውቋል፡፡
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ “የተጠቂዎች ማንነት እንዲሁም የኤርትራ ወታደሮች ሚና”ን በተመለከተ በሰጠው መግለጫ ልዩነት አለኝም ነው ያለው አምነስቲ፡፡
እንደ ዓለም አቀፉ ተቋም ገለጻ ከሆነ በአክሱም ተፈጸመ በተባለው ወንጀል በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሀን ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከቀናት በፊት ለመገናኛ ብዙሀን በሰጠው መግለጫ በአክሱም በነበረው ውጊያ 93 ሰዎች መሞታቸውንና “ሟቾቹ ወታደራዊ የደንብ ልብስ ባይለብሱም አብዛኞቹ በጦርነቱ የተሳተፉ መሆናቸውን በምርመራው መረጋገጡን” አስታውቋል፡፡
በምርመራው “በጦርነቱ ተሳትፎ ያልነበራቸው በመንገድ ላይ የነበሩ ንጹሀን” ጭምር መግደላቸውንም ነው ዐቃቤ ህግ ያስታወቀው፡፡
“የለም ጥቃቱ ያነጣጠረው በታጣቂዎች ላይ ሳይሆን ንፁሀን ላይ ነው” ያለው አምነስቲ ኢንትርናሽናል ግን የዐቃቤ ህግን መግለጫ ተቃውሟል፡፡
“ከሞት ለማምለጥ ሲሞክሩ የነበሩ ያልታጠቁ ንፁሀን መጠቃታቸውን በምርመራ አረጋግጫለሁኝ”ም ነው አምነስቲ ያለው፡፡
በኤርትራ ሰራዊት ሲደረግ በነበረው የቤት ለቤት አሰሳ ወጣቶችና አዛውንቶችን ጨምሮ በርካታ ንጹሀን ተገድለዋል ያለው አምነስቲ እስከ አመሻሽ በቆየው የቤት ለቤት አሰሳ “በርካቶች ቤተሰቦቻቸው ፊት ተረሽነዋል” ሲል አክሏል፡፡
ወንጀሉን በመፈጸም ረገድ የኤርትራ ሰራዊት ሚናን በተመለከተም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በልኩ አላስቀመጠም ሲልም ተችቷል፡፡
የህወሓት ታጣቂዎች በኤርትራ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈፀማቸው እንዲሁም በእስር ለነበሩ ወንጀለኞች የኤርትራ ወታደራዊ የደምብ ልብስ በመስጠት ከእስር ቤት መልቀቃቸው በአክሱም ለተፈፀመ ድርጊት ምክንያት እንደሆነ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መግለፁ የሚታወስ ነው፡፡
ይሁን እንጅ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከምስክሮች በቃለ መጠይቅ አረጋገጥኩት እንዳለው ከሆነ “የቤት ለቤት አሰሳ ሲያካሂዱ የነበሩት የኤርትራ ወታደሮች ከለበሱት የደምብ ልብስ በተጨማሪ በባህል እና የቋንቋ ዘያቸው ይለያሉ” ብሏል፡
በመግለጫው ማጠቃለያም “በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ጭፍጨፋ የመመርመር ኃላፊነት” እንዳለበት አስቀምጧል፡፡
አምነስቲ ምንም እንኳን መሰል ምርመራዎች በአለም አቀፍ አሰራር ፈጣን፣ የተሟሉ፣ ውጤታማ፣ ገለልተኛ እና ግልጽነት ያላቸው መሆን ቢጠበቅባቸውም፤ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ያደረገውን ምርመራ በመርህ ደረጃ እንደሚቀበል አስታውቋል፡፡
ሆኖም ከመርሆቹ በመነሳት በተለይም የምርመራው ነፃነት እና ገለልተኛነት እንደሚያሳስበውና የምርመራ ግኝቶቹ ተዓማኒ እንዳይደሉም ገልጿል፡፡
በመሆኑም የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መግለጫ የኤርትራ ወታደሮች የነበራቸውን ሚና በመቀነስ ጭፍጨፋውን ለመሸፋፈን ያለመ ነው ብሏል አምነስቲ፡፡
አምነስቲ ለወደፊት ሊከሰሱ በሚችሉ አካላት ላይ ማስረጃዎች የመሰብሰብ ስልጣን ባላቸው ገለልተኛ ዓለም አቀፍ ወይም አህጉራዊ ተቋማት ምርመራ እንዲደረግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡