11ኛ ክልል ለመመስረት ነገ በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ውሳኔ ይደረጋል
ሕዝበ ውሳኔው በከፋ፣ ዳውሮ፣ ቤንች ሸኮ፣ ምዕራብ ኦሞና የሸካ ዞኖች እንዲሁም የኮንታ ልዩ ወረዳ ነው የሚደረገው
ሕዝበ ውሳኔው ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ምርጫ ባልተደረገባቸው አካባቢዎች ከሚደረግ ምርጫ ጋር አብሮ ነው የሚካሄደው
ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ባለው አዲስ አወቃቀር መሰረት በኢትዮጵያ 11ኛ ክልል ለመመስረት ነገ ሕዝብ ውሳኔ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያወጣው የጊዜ ሰሌዳ ይጠቁማል።
ጳጉሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔ ነገ ከሌላ መርሃ ግብር ጋር እንደሚካሄድ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ቦርዱ፤ ነገ የሚደረገው ሕዝበ ውሳኔ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ምርጫ ባልተደረገባቸው አካባቢዎች ከሚደረግ ምርጫ ጋር አብሮ እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡
በዚህም መሰረት ነገ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔ ሲካሄድ በሶማሌ፣ በደቡብ ክልል በተለያዩ ወረዳዎች እና በሀረሪ ክልሎች ምርጫ ይካሄዳል።
መጀመሪያ ላይ ሕዝበ ውሳኔው ሰኔ 14 ከሀገር አቀፉ ምርጫ ጋር ይካሄዳል ቢባልም በኋላ ላይ በተደረገ የጊዜ ሰሌዳ ማሸጋሸግ ጳጉሜ 1 ቀን 2013 እንዲካሄድ ተወስኖ ነበር።
ሕዝበ ውሳኔው የሚደረግባቸው አካባቢዎች አስተዳደሮች በመራዘሙ ቅሬታ አቅርበው እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፤ ቦርዱ ከመራጮች ምዝገባ ጋር ተያይዞ የተነሱትን ጥያቄዎችን ለመፍታት ጊዜ ስለሚያስፈልግ ምርጫውን እና የሕዝበ ውሳኔውን ማራዘም ማስፈለጉን መግለጹ ይታወሳል።
ሕዝበ ውሳኔ የሚደረግባቸው አካባቢዎች የከፋ፣ ዳውሮ፣ ቤንች ሸኮ፣ ምዕራብ ኦሞና የሸካ ዞኖች እንዲሁም የኮንታ ልዩ ወረዳ ናቸው።
አምስቱ ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ በአንድ ክልል ስር ለመደራጀት ያቀረቡት ነገ በሚካሄድ ምላሽ ያገኛል ተብሏል። አካባቢዎቹ በአንድ ክልል ስር ለመደራጀት ጥያቄ ማቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን ክልል ለመሆን የሚያስፈልገው የሕግ ሂደት ብቻ ነው ተብሏል።
ነገ በሚደረግ ሕዝበ ውሳኔ ይዋቀራል ተብሎ ለሚጠበቀው “የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል” ሕገ መንግስት እየተዘጋጀለት መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ሕዝበ ውሳኔ ማስፈጸሚያ ፕሮጄክት ጽ/ቤት ለአል ዐይን አማርኛ መግለጹ ይታወሳል።
የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ስራ አስኪያጅ ምትኩ በድሩ (ኢ/ር)፣ ከወራት በፊት ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ አዲስ ይዋቀራል ተብሎ ለሚጠበቀው ክልል የሰነድ ስራዎች እየተዘጁለት መሆኑን ገልጸዋል።
ምንም እንኳን የሕዝበ ውሳኔው ውጤትና አጠቃላይ ዝግጅቱ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚመራና የሚገለጽ ቢሆንም በሕዝበ ውሳኔው ውጤት ክልሉ የሚመሰረት ከሆነ በሚል ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን መገለጹ ይታወሳል። የክልል ስያሜ ፣ ሰንደቅ ዓላማ ፣ የሥራ ቋንቋና ሌሎችም ጉዳዮች የሚካተቱበት ሕገ መንግስት እየተዘጋጀ እንደሆነም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝበ ውሳኔ የምርጫ ምልክትን ቀደም ብሎ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
አምስቱ ዞኖችና አንዱ ልዩ ወረዳ የጋራ አንድ ክልል መመስረታቸውን እደግፋለሁ የሚለው በተያያዙ እጆች የሚወከል ሲሆን የጎጆ ቤት ምልክት ደግሞ አካባቢዎቹ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል አካል ሆነው መቀጠላቸውን እደግፋለሁ የሚለውን ለመምረጥ ይፋ የተደረጉ ምልክቶች ናቸው።