አብዲ ኢሌና ሜ/ጀ ክንፈ ዳኘው በሽብርና በሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው እንደነበረ ይታወሳል
የፍትህ ሚኒስቴር በእነ አብዲ ሞሃመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ) እና በእነ ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘው መዝገቦች ቀርበው የነበሩ ክሶች እንዲቋረጡ መወሰኑን አስታወቀ።
የፍትህ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ፤ ክሶቹ እንዲቋረጡ የተደረጉት ለህዝብ ጥቅም ሲባል” ነው ብሏል።
የሶማሌ ክልል የቀድሞ ርዕሰ መስተዳድር አብዲ ሞሃመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ) የክስ መዝገብ በ1ኛ የህገ-መንግስትና የሽብር ወንጀል ጉዳዮች ችሎት የክርክር ሂደት ላይ መቆየቱ የሚታወቅ ነው።
የሶማሌ ክልል የቀድሞ ርዕሰ መስተዳድር አብዲ ሞሃመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ) በ2011 ዓ.ም በክልሉ የተፈጠረውን ሁከት ተከትሎ በቁጥጠር ስር መዋላቸው ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎም የሶማሌ ክልል የቀድሞ ርዕሰ መስተዳድር አብዲ ሞሃመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ) የህገ-መንግስትና የሽብር ወንጀል ጉዳዮች ችሎት የክርክር ሂደት ላይ የቆዩ ሲሆን፤ በዛሬው እለትም ከሱ እንዲቋረጥ ተወስኗል።
በእነ ሜ/ጀ ክንፈ ዳኘው መዝገብ ስር ያሉ ተከሳሾች በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሙስና ወንጀል ክስ ክርክር ሲካሄድ የነበረ መሆኑ ይታወቃል።
ቀድሞ የኢትዮጵያ ብረታ ብረት እና ኢነጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዲሬክተር ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው በህዳር ወር 2011 ዓ.ም በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።
ከኮርፖሬሽኑ ሥራ ጋር በተያያዘ በከባድ የሙስና ወንጀል የሚጠረጠሩት ጀነራል ክንፈ በምዕራባዊ ትግራይ በኩል ባታር በተሰኘው አካባቢ ተይዘው መታሰራቸውም በወቅቱ መገለጹ አይዘነጋም።
ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ከራዳር እቃዎች የግዥ ሒደት ጋራ ተያይዞ በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ ተብለው የ3 ዓመት ከ7 ወር እስራት ቅጣት ተወስኖባቸውም ነበር።