ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) በመታወቂያ ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ ተወሰነላቸው
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ከሁለት ወር በፊት ምሽት ላይ ነበር ከመኖሪያ ቤታቸው በጸጥታ ሀይሎች የተወሰዱት
ሌላኛው የፓርቲ አጋራቸው አቶ ክርስቲያን ታደለ ከታሰሩ ሰባት ወራት በኋላ ያለመከሰስ መብታቸው መነሳቱ ይታወሳል
ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) በመታወቂያ ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ ተወሰነላቸው፡፡
በ2013 በተካሄደው ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በባህርዳር ከተማ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲን ወክለው ተወዳድረው የተመረጡት እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ታህሳስ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ታስረው ነበር፡፡
ጠበቃቸው ሰለሞን ገዛኸኝ ለአልዐይን እንዳሉት ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት በመታወቂያ ዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ ተነግሯቸዋል፡፡
ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት ከእስር ተለቀው ከቤተሰቦቻው ጋር መቀላቀላቸውንም ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ አክለዋል።
ባሳለፍነው ሀምሌ ወር ላይ በተመሳሳይ ከመኖሪያ ቤታቸው በጸጽታ ሀይሎች ተወስደው በእስር ላይ የነበሩት ሌላኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ ያለመከሰስ መብታቸው ከታሰሩ ከሰባት ወራት በኋላ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተነስቷል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊትም የአዲስ አበባ እና አማራ ክልል ምክር ቤቶች የካሳ ተሻገር (ዶ/ር) እና አቶ ዮሀንስ ቧያለው ያለመከሰስ መብታቸውን ማንሳታቸው አይዘነጋም፡፡
ባሳለፍነው ዓመት ሚያዚያ ወር የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሼ ለማደራጀት ወስኛለሁ ማለቱን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል ግጭት የተከሰተው፡፡
ይህ ግጭት ቀስ በቀስ እያደገ መጥቶ ወደ ጦርነት የተቀየረ ሲሆን የቀድሞው የክልሉ መንግስት በመደበኛ የክልሉ የጸጥታ ሀይል ህግ ማስከበር እንደማይችል እና የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ በይፋ በደብዳቤ ጠይቋል፡፡
ይህን ተከትሎም ከሀምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀ ቢሆንም አዋጁ ለተጨማሪ አራት ወራት ተራዝሟል፡፡