የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ ታየ ደንደአ ባሳለፍነው ታህሳስ ወር ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ መታሰራቸው ይታወሳል
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ ታየ ደንደአ ያለመከሰስ መብት ተነሳ።
ጨፌ ኦሮሚያ በካሄደው መደበኛ ስብሰባው ላይ ነው የምክር ቤቱ አባል የነበሩትን የአቶ ታየ ደንደአን ያመለከሰ መብት ማንሳቱ የተገለጸው።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባወጣው መረጃ በክልሉ ህገ መንግስት አንቀጽ 48 ንዑስ አስቀጽ 6 መሰረት ማንኛውም የጨፌው አባል በመረጠው ህዝብ ዘንድ ተዓማመኒነት በሚያጣበት ጊዜ ከምክር ቤቱ እንደሚሸኝ ተደንግጓል ብሏል።
በዚሁ መሰረት ጨፌ ኦሮሚያ በዛሬው እለት እያካሄደ ባለው መደበኛ ስብሰባው ላይ በአቶ ታየ ደንደአ ያለ መከሰስ መብትን ማነሳት ላይ ከተወያየ በኋላ ማጽደቁን አስታውቋል።
ጨፌው የአቶ ታዬ ደንደአን ያለመከሰስ መብትን በ439 ድጋፍ እና በ14 ድምፀ ታቅቦ በአብላጫው ድምፅ አፅድቋል፡፡
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ ታየ ደንደአ ባሳለፍነው ታህሳስ ወር ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።
አቶ ታየ ደንደዓ በመንግስት እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል ሲደረግ ስለነበረው ድርድር ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት አስተያየት መንግስታቸውን ተጠያቂ ማድረጋቸው ይታወሳል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተጻፈ ደብዳቤ ከሀላፊነታቸው እንደተነሱ መነገሩ የሚታወስ ሲሆን፤ አቶ ተየ አንደአም በወቅቱ በማሀበራዊ ትስስር ገጻቸው “የወንድማማቾች መገዳደል ይቆም ዘንድ ለሰላም በመወገኔ ከስልጣን አነሱኝ” ብለው ነበር።
ይህንን ተከትሎም የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ባወጣው መግለጫ፤ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት ታየ ደንደአ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ማስታወቁ አይዘነጋም።
ግብረ ኃይሉ በመግለጫው አቶ ታየ ደንደአ፤ "በመንግስት ቁጥጥር ስር ሊዉል እንደሚችል ሲገምት ታጋይ ለመምሰል በራሱና በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጾች አፍራሽና ፀረ ሰላም ፅሁፎችን፣ ንግግሮችንና መግላጫዎችን በማን አለብኝነት ሲያስተላልፍና ሲሰጥ ቢቆይም ከተጠያቂነት ማምለጥ ባለመቻሉ በጋራ ግብረ ኃይሉ በቁጥጥር ስር ውሏል" ብሏል።
“በተለያዩ አካባቢዎች በንፁሃን ዜጎች ላይ ሲፈፀሙ በነበሩ የሽብር ተግባራት በተለይም ደግሞ ከእገታ ጋር በተያያዘ እጁ እንዳለበት ተደርሶበታል” ብሏል ግብረ ኃይሉ በመግለጫው ።