የአቶ ክርስቲያን ታደለ ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ መታሰራቸው ይታወሳል
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባው የምክር ቤቱ አባል የሆኑትን የአቶ ክርስቲያን ታደለ ፀጋዬን ያለመከሰስ መብት አንስቷል።
ምክር ቤቱ በዛሬው እለት ባካሄደው 17ኛ መደበኛስብሰባው ነው የምክር ቤቱ አባል የሆኑትን የአቶ ክርስቲያን ታደለን ያለመከሰስ መብት ያነሳው።
በምር ቤቱ ተገኝተው የምክር ቤት አባሉን ያለመከሰስ መብት መነሳት አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት የፍትህ ሚንስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን አቶ ክርስቲያን በአማራ ክልል ሕገመንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ ከሚንቀሳቀሱ አካላት ጋር አብረው ሲሰሩ እንደነበር ብለዋል።
ይህንን ተከትሎም ምክር ቤቱ የአቶ ክርስቲያን ታደለ ያለመከሰስ መብት በሁለት ተቃውሞ እና በሁለት ድምጸ ተዐቅቦ እንዲነሳ ወስኗል።
ምክር ቤቱም በውሳኔ ቁጥር 9/16 የአቶ ክርስቲያን ታደለን ያለመከሰስ መብት ማንሳቱንም ነው ያገኘነው መረጃ የሚያመለክተው።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩት የነበሩት የአቶ ክርስቲያን ታደለ ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ መታሰራቸው ይታወሳል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባሳለፍነው ህዳር ወር በሰጠው መግለጫ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን(አብን) በመወከል የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ማሳወቁም አይዘጋም።
በአማራ ክልል ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የሚገኙት ብልጽግና ፖርቲን በመወከል የአዲስ አበባ ምክርቤት አባል የሆኑት ዶ/ር ካሳ ተሻገር ያመለከሰስ መብትም በቅርቡ መነሳቱ ይታወሳል።
በተጨማሪም የአማራ ክልል ምክር ቤት ባሳለፍነው የካቲት ወር ላይ ክልሉ ምክር ቤት አባል የነበሩትን የአቶ ዮሐንስ ቧያለውን ያለመከሰስ መብት ማንሳቱም አይዘነጋም።
በተያያዘ በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲን ወክለው ተወዳድረው የተመረጡት እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) መታሰራቸውም ይታወቃል።
ባሳለፍነው ዓመት ሚያዚያ ወር የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሼ ለማደራጀት ወስኛለሁ ማለቱን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል ግጭት የተከሰተው።
ይህ ግጭት ቀስ በቀስ እያደገ መጥቶ ወደ ጦርነት የተቀየረ ሲሆን የቀድሞው የክልሉ መንግስት በመደበኛ የክልሉ የጸጥታ ሀይል ህግ ማስከበር እንደማይችል እና የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ በይፋ በደብዳቤ ጠይቋል።
ይህን ተከትሎም ከሀምሌ 2015 ዓ.ም መጨረሻ ቀናት ጀምሮ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀ ሲሆን፤ ይህንን ተከትሎ የፌደራል እና የክልል ምክር ቤት አባልትነ ጨምሮ በርካቶች በቁጥጥር ስር ውለዋል።