በሰሜን ጎንደር ዞን በመሬት መንሽተት አደጋ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 23 ደረሰ
በዞኑ ጠለምት ወረዳ ብቻ በመሬት መንሸራተት አደጋ 10 ሰዎች ሞተዋል
በዞኑ 4 ወረዳዎች ባጋጠመው የመሬት መንሸራተት አደጋ ከ2 ሺህ 700 በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል
በአማራ ከልል ሰሜን ጎነደር ዞን አራት ወረዳዎች ከሰሞኑ በደረሱ የመሬት መንሸራተት አደጋዎች የሞቱ ሰዎች ቁጥር 23 መድረሱ ተገለጸ።
በወረዳዎቹ በደረሰው አደጋ የ23 ሰው ህይወት ከማለፉም በተጨማሪ ከ2 ሺህ 700 በላይ ነዋሪዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ሰላምይሁን ሙላት እንደተናገሩት፤ አደጋው የደረሰው በዞኑ በጠለምት፣ በጃናሞራ፣ በአዲአርቃይና በየዳ ወረዳዎች በሚገኙ 11 የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ ነው።
በጠለምት ወረዳ ብቻ በመሬት መንሸራተት አደጋ የ10 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፤ 8 ሰዎች ደግሞ አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸውበአካባቢው የጤና ተቋማት የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑ ተመልክቷል።
በወረዳው ከ35 በላይ የቤት እንሰሳት መሞታቸውን እና ከ30 ሔክታር በላይ በሰብል የተሸፈነ መሬትም ከጥቅም ውጭ መሆኑም ተነግሯል።
በአራቱ ወረዳዎች በመሬት መንሸራተት አደጋው በ1 ሺ 775 ሄክታር ላይ የተዘራ ሰብል መውደሙን ጠቅሰው፤ 48 መኖሪያ ቤቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው ከዞኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በአሁኑ ወቅት የጉዳቱ ሰለባ ለሆኑ ቤተሰቦች የእለት ምግብ እርዳታን ጨምሮ የመጠለያ አገልግሎት እንዲያገኙ ግብረ ሃይሉ የአካባቢውን ህብረተሰብ በማስተባበር ሰፊ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።