ትዕዛዞችና ክልከላዎችን በሚጥሱ አካላት ኃይልን ጨምሮ ሌሎች አግባብነት ያላቸውን እርምጃዎችን እወስዳለሁ ብሏል
የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ "በመጀመሪያው ምዕራፍ ዕቅድ" መገባደዱን ተከትሎ በስድስት የአማራ ክልል ከተሞች አዲስ ትእዛዝና እግድ አውጥቷል።
ዕዙ ነሀሴ 03 በሰጠው መግለጫ ባህር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ጎንደር፣ ላሊበላ፣ ደብረ ብርሀንና ሸዋ ሮቢት ከተሞች "ከታጣቂዎች ስጋት ነጻ" መሆናቸውን አስታውቋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምን አዲስ ውሳኔ አሳለፈ?
1. ከዛሬ ሀሙስ ነሀሴ 04 ጀምሮ በስድስቱ ከተሞች መደበኛ የአውሮፕላን በረራ ይጀመራል፤
2. ከባጃጅና ከሞተር ሳይክል በስተቀር ሁሉም አይነት የከተማ የትራንስፖርት አገልግሎቶች ወደ አገልግሎት ይገባሉ፤
3. የመንግስት፣ የማህበረሰብ አገልግሎት፣ የንግድ፣ የጤና፣ የፋይናንስ፣ ወዘተ. ተቋማት አገልግሎት እንዲሰጡ፤
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምን አዲስ እግድ አወጣ?
1. በባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ብርሃን፣ ደብረ ማርቆስ፣ ሸዋ ሮቢትና ላሊበላ እስከ ነሐሴ 17፣2015 የሚቆይ የሠዓት እላፊ ገደብ ተጥሏል፡
በዚህም መሰረት የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ከሚሰጡ ተሽከርካሪዎች፣ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ሰጪ ባለሞያዎች እና የጸጥታ አስከባሪ ተቋማት ባልደረቦች ውጪ ለማንኛውም ሰው እና ተሽከርካሪ ከምሽቱ አንድ ሰዓት በኋላ መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ነው።
2. የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ ፈቃድ ውጪ በአማራ ብሔራዊ ክልል ከተሞች የአደባባይ ስብሰባ፣ ሰልፍ እና መሰል እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ፈጽሞ የተከለከለ ነው።
እንዲሁም በማንኛውም መልኩ የህዝብ እንቅስቃሴን የሚያስተጓጉል እና የትራንስፖርት አገልግሎትን የሚያሰናክል ድርጊት በጥብቅ የተከለከለ ነው።
3. በአማራ ብሔራዊ ክልል ለጸጥታ ስራ ከሚንቀሳቀሱ የህግ አስከባሪ አካላት እና ከነዚህ አካላት ፈቃድ ውጭ የጦር መሣሪያ ይዞ መዘዋወር ፈጽሞ የተከለከለ ነው።
4. በአማራ ብሔራዊ ክልል (በስድስቱ ከተሞች) የባጃጅ እና የሞተር ሳይክል እንቅስቃሴ ከነሀሴ 04 እስከ ነሐሴ 17፣2015 ድረስ ፈጽሞ የተከለከለ ነው።
5. ከባጃጆችና ከሞተር ሳይክሎች በስተቀር ሌሎች የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ከነሀሴ 04 ጀምሮ ወደ ስራ የመመለስ እና አገልግሎት የመስጠት ግዴታ አለባቸው።
6. በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሽፋን ከአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ትእዛዝ ውጭ ወቅታዊ ሁኔታን ሰበብ በማድረግ ግለሰቦችን ከመደበኛው ህግ አግባብ ውጪ ማሰር እና ማቆየት፣ የንግድ ቤቶችን ማሸግ እና መሰል እርምጃዎችን መውሰድ በጥብቅ የተከለከለ ነው።
ትዕዛዞችና ክልከላዎችን በሚጥሱ ላይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኃይልን በመጠቀም፣ እንዲሁም ሌሎች አግባብነት ያላቸውን እርምጃዎችን በመውሰድ ትዕዛዝና ክልከላዎችን እንዲያስፈጽሙ ለሁሉም የህግ አስከባሪ አካላት ጥብቅ መመሪያ መስጠቱንም አስታውቋል።