ኢትዮጵያና ቻይን በኮረና ቫይረስ ዙሪያ ምን ተባባሉ?
የግማሽ ከፍለ ዘመን ወዳጅነት
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂሩት ዘመነ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ረዳት ሚኒስትር ቼን ሽያዶነግን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው በሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ የተመካከሩ ሲሆን በወቅታዊው የኮሮና ወረርሽኝና በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይም መምከራቸው ተሰምቷል፡፡
ወ/ሮ ሂሩት ኢትዮጵያ እና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 50ኛ ዓመት ለማክበር በዝግጅት ላይ የሚገኙ መሆናቸውን በማስታወስ በአሁኑ ስዓት የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ከመቼውም ጊዜ በላይ በተጠናከረ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ታሪካዊ፣ ሁሉን አቀፍ፣ ውጤታማ፣ በተግባር የተደገፈ፣ ተገማች እና ስትራቴጂያዊ መሆኑን ያነሱት ወ/ሮ ሂሩት ይኸው ግንኙነት በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። ሁለቱ አገሮች ከሁለትዮሽ በተጨማሪ በዓለም አቀፍ መድረኮች የሚያደርጉትን ግንኙነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ የገለጹት።
ኢትዮጵያ እና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 50ኛ ዓመት በሚያከብሩበት በዚህ ወቅት በሁለቱ አገሮች ትብብር እየተከናወኑ ያሉ በርከታ ፕሮጀክቶች በውጤት እንዲጠናቀቁ አስፈላጊው ክትትል እና ድጋፍ እንደሚደረግም ቼን አረጋግጠዋል። ሁለቱ አገሮች በቻይና አፍሪካ ትብብር፣ በተባበሩት መንግስታት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ መድረኮች የሚያደርጉትን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው ረዳት ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡
ኮሮና፣ኢትዮጵያና ቻይና
በአሁኑ ስዓት በቻይና የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር ቻይና ሙሉ አቅም እና ብቃት እንዳላት ኢትዮጵያ እምነቷ መሆኑን የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂሩት ዘመነ ገልጸዋል፡፡
ወረርሽኙ ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት በመሆኑ ኢትዮጵያ እንደ ወትሮው ሁሉ ከቻይና ጎን በመቆም ወረርሽኙን ለመከላከል አስፈላጊውን ትብብር እንደምታደርግም ነው ወ/ሮ ሂሩት ያስታወቁት፡፡ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው መመሪያ መሰረት ኢትዮጵያ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረገች መሆኗንም ሚኒስትር ዴኤታዋ አብራርተዋል፡፡
ቼን ሽያዶነግ በበኩላቸው ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት ልዩ ትኩረት እንደምትሰጥ በመግለጽ፣ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ያስተላለፉትን መልዕክት በማንሳት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የቻይና መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እና ለመቆጣጠር አገር አቀፍ ስርዓት መዘርጋቱን እና በሽታውን ለመቆጠጣር የሚያስችል ሙሉ አቅም እንዳለውና ቁርጠኝነት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ቻይና ከዓለም መንግስታት እና ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር በቅርበት እና በትብብር እየሰራች መሆኑን ያስታወሱት ቼን ሽያዶነግ ቫይረሱን በዘላቂነት ለመቆጣጠር የሚያስችል መፍትሄ በቅርቡ ማግኘት እንደሚቻል እምነታቸው መሆኑንም ገልጸዋል። በቻይና የሚኖሩ ኢትጵያዊያንን እና ሌሎች የውጭ ዜጎችን ደህንንት ለመጠበቅ አስፈላጊው ጥንቃቄ እና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ረዳት ሚኒስትር ቼን ገልጸዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በድረ ገጹ ይፋ እንዳደረገው።