ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ዛሬ ምን አሉ?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ዛሬ ምን አሉ?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከአባላቱ ለተነሱላቸው ጥያቄ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለጥያቄዎቹ መልስ ከመስጠታቸው በፊት ኢመደበኛ ትስስሮች የመንግስትን የመፈጸም አቅም እየተፈታተኑት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
መረቡን ለመበጣጣስ ቢሞከርም እስከታችኛው የመንግስት መዋቅር ድረስ የተዘረጋ በመሆኑ በጥሶ ለማጥፋት እንዳልተቻለ እና ይህም መንግስትን በቁጥጥር ስር እንዳደረገው ነው የተናገሩት፡፡ በዘርና በጥቅም የተሳሰረውን መረብ መለየትና መፍቻ ቁልፉን ማግኘቱም ቀላል አይደለም ብለዋል፡፡
የታገቱ ተማሪዎች
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በእገታው ምክንያት የሞተ ሰው የለም ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት መካለከያ ባደረገው አሰሳ “እሳከሁን የተገደለ ሰው የለም፤ ተጎድቶ የተገኘ የለም፡፡ ችግር አልደረሰባቸውም እንዳንል ደግሞ ቤተሰብ ጋር አልደረሱም፡፡ ” መከላከያ ባደረገው በአሰሳው መሰረት መንግስት የታገቱ የሉም ለማለት የሚያስችል መረጃ ነበር፣ ነገር ግን “አልታገቱም “ የሚል መልስ መስጠት አልቻልንም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡፡
አጋቾቹ የውጭ ሳይሆን የውስጥ ጠላት መሆናቸው ፍለጋውን እና ታጋቾቹን የማስለቀቅ ስራውን ከባድ አድርጎታልም ነው ያሉት፡፡ እርምጃ እየወሰድን ዝምታን የመረጥነው ማንም ሰው ሳይሞት በህይወት ለማግኘት ስለምንፈልግ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የምርጫ ጉዳይ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የምርጫ ጉዳይ ከመንግስት ይልቅ ምክር ቤቱን የሚመለከት ነው ብለዋል፡፡ ቦርዱ የምርጫ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁን ለምክር ቤቱ እንጂ ለመንግስት አላቀረበም ያሉም ሲሆን ለተቋማዊ ለውጡ ስኬት ቦርዱ በጠየቀው መሰረት ከማገዝ ውጭ በህግ ጉዳይ እጃችንን አላስገባንም ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የቀረበውን ጊዜያዊ የምርጫ ሰሌዳ ቦርዱ ከፓርቲዎች ጋር ተነጋግሮ ሊያሻሽለው እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡ሆኖም የተሟላ ሰላም መቼ እንደሚገኝ የማይታወቅ በመሆኑ ምክር ቤቱን ጨምሮ ሁሉም ሊደግፍ ይገባል ብለዋል፡፡
የህወሐት አባላት ከፌዴራል ስልጣን መነሳት
የትግራይን ህዝብ ያገለለ መንግስት መመስረት አይቻልም፤ የትግራይ አመራሮች ከፌዴራል መንግስቱ እየተገፉ ነው መባሉ ተገቢነት የለውም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)፡፡ ከሰሞኑ አንድ ሚኒስትር መነሳታቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ ጉባዔን ጨምሮ ሌላ አንድ ሚኒስትር እና16 ሚኒስትር ዴዔታዎች በካቢኔ አባልነትም ጭምር ከፍተኛ አመራሮች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ ሕወኃት ለረዥም ጊዜ አብሮን የነበረና ወደፊትም አብረን ልንሰራ የምንችል ስለሆነ ያን አናደርግም ያሉም ሲሆን ገዢው ፓርቲ ብልጽግና እንደሆነ እና የራሱን ካቢኔ ማዋቀር እንደሚችል መረሳት እንደሌለበት እንዲሁም የትግራይን ህዝብ ያገለለ መንግስት መመስረት እንደማይቻል አስታውቀዋል፡፡
የደቡብ ክልል “እንሁን ጥያቄ”
በደቡብ ክልል ከፍተኛ የልማትና የፖለቲካ ጥያቄዎች አሉ፤ ሁለቱ ጥያቄዎች ግን አብረው አይሄዱም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡፡ ክልል፣ዞንና ወረዳ ሲበዛ ደሞዝተኛ ይበዛል እንጂ የህዝብ ጥያቄ አይመለስም ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ልማቱን ፖለቲካው እንዳይጨፈልቀው የደቡብ ክልል ህዝቦች መወያየት አለባቸው ብለዋል፡፡ ክልል መሆንን ራስን በራስ ከማስተዳደር ጋር እንድ አድርጎ የማየት ችግር አለ፤ ያሉት ዶ/ር ዐቢይ ሰው በዞንም በወረዳም ህገመንግሰታዊ መብቱን ማስከበር እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
“ህዝቡ እንዲገነዘብ የምፈልገው መንግስት ደቡብ ክልል ተጨፍልቆ አንድ ካልሆነ የሚል አቋም የለውም፤ ደቡብ ተሸንሽኖ 10 ካልሆነ የሚለውን ግን ለመወሰን” ህዝቡ ጥቅምና ጉዳቱን ማስላት አለበት ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡፡
የህዳሴው ግድብ ድርድር
ታላቁን የህዳሴ ግድብ በሚመለከት ኢትዮጵያ ጥቅሟን አሳልፋ እንደማትሰጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ድርድር ሳይቋጭ ዘላቂ ጥቅም አስከብሪያለሁ ወይም አላስከበርኩም ማለት ትርጉም የለውም ብለዋል፡፡ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ካለባቸው ስጋት አንጻር መሰረታዊ ጥያቄ አላቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለፉት 8 ዓመታት ድርድር አታካች እንደነበረም ጠቁመዋል፡፡ ሶስት ሆነን ስንነጋገር ያልተግባባንባቸውን ብዙ ጉዳዮች በአሜሪካና ዓለም ባንክ ፊት ተስማምተናል በማለት ሁለቱን አካላትም አመስግነዋል፡፡
በአሜሪካ በነበረው የመጨረሻ ድርድር የመጨረሻ ፊርማ ከመፈረማቸው በፊት በኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች መረጃ ተሰጥቷቸው ፊርማው እንዲቆይ ማድረጋቸውንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተናገሩት፡፡ ከየትኛውም የዓለም መንግስት ጋር ስንነጋገር ቀዳሚ ሆኖ የሚነሳው ጉዳይ ይሄው የግድብ ጥያቄ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ“ኢትዮጵያን በሚጎዳ ነገር ላይ የሚወስን መንግስት እስካሁን አልነበረም ወደ ፊትም አይኖርም” ብለዋል፡፡
የስራ እድል ፈጠራ
የስራ እድል ፈጠራን በተመለከተ በተያዘው ዓመት 3 ሚሊዮን ስራ ለመፍጠር የተለጠጠ እቅድ ተይዞ እስካሁን በ6 ወር 1.2 ሚሊዮን ወጣት ስራ ተፈጥሮለታል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ከነዚህም 65 በመቶው ቋሚ ቀሪው 35 በመቶ ደግሞ ጊዜያዊ የስራ እድል የተፈጠረላቸው ናቸው፡፡ ይሄም በፊት ከነበረው አንጻር ከፍተኛ ለውጥ ሲሆን ካለብን ድህነትና ስራ አጥነት አንጻር ግን ዝቅተኛ ነው ብለዋል፡፡ የስራ እድል ከመፍጠር አንጻር መንግስት ወደፊትም የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡