የህዳሴ ግድብን የተመለከተው የመጨረሻው ስምምነት የካቲት ላይ ይፈረማል
የህዳሴ ግድብን የተመለከተው የመጨረሻው ስምምነት የካቲት ላይ ይፈረማል
የኢትዮጵያ፣የግብጽ እና የሱዳን የውጭ ጉዳይና የውሃ ሚኒስትሮች እና የልዑኮቻቸው በአሜሪካ በታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሲያካሄዱት የነበውን ውይይት አጠናቀዋል፡፡
በአሜሪካ ግምጃ ቤትና በዓለም ባንክ ታዛቢነት በዋሽንግተን ሲካሄድ የነበረው ውይይት ተጠናቋል፡፡
የውይይቱን መጠናቀቅ በማስመልከትም የጋራ መግለጫ ወጥቷል፡፡
እንደመግለጫው ከሆነ በውይይቱ ማጠቃለያ የሶስቱ ሀገራት ሚኒስትሮች በሶስት ቀዳሚ ጉዳዮች ላይ ማለትም በግድቡ የሙሌት ሰንጠረዥ፣ በድርቅ፣በተራዘመ ድርቅ እና በተራዘሙ ደረቃማ አመታት በሚኖሩበት ጊዜ የግድቡ የሙሌት ሁኔታዎች እና በድርቅ፣በተራዘመ ድርቅ እና በተራዘሙ ደረቃማ አመታት በግድቡ አመታዊና የረጅም ጊዜ ኦፐሬሽን ላይ ከስምምነት ደርሰዋል፡፡
ሆኖም ስምምነቱ የሃገራቱን የመጨረሻ ፊርማ የሚጠብቅ ነው፡፡
ግድቡ በመደበኛ የውሃ ፍሰት ሁኔታዎች ስለሚኖረው አመታዊና የረጅም ጊዜ የትግበራ ሂደት፣ የትብብር እና የልዩነት መፍቻ መንገዶችን እንዲሁም የመረጃ ልውውጥን የተመለከቱ ጉዳዮችን ለማጠቃለልም ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
የግድቡን ደህንነት እና ሊኖረው የሚችለውን አካባቢያዊና ማህበራዊ ተጽዕኖዎች ለማጥናት ለሚደረጉ ጥረቶች ምላሽ ለመስጠትም ተስማምተዋል፡፡
ሚኒስትሮቹ እነዚህን ጨምሮ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የካቲት አጋማሽ ላይ የሚፈረመውን የመጨረሻውን ስምምነት እንዲያዘጋጁ ለቴክኒክ እና የህግ ቡድኖቻቸው ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡
ስምምነቱ ሊኖረው ስለሚችለው ጥቅም እውቅና የሰጡት ሚኒስትሮቹ ግድቡ ለቀጣናዊ ትብብር እና ልማት እንዲሁም ለምጣኔ ሃብታዊ ውህደት የጎላ አበርክቶ እንደሚኖረውም አልሸሸጉም፡፡
ድንበር ተሻጋሪውን አባይን በጋራ ማልማቱ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል እንደሚያስችልም ሚኒስትሮቹ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡