የግድቡ የዉሃ ሙሌት መጀመሩን የዉሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ገልጸዋል
የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ደረጃ የዉሃ ሙሌት ተጀመረ
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ደረጃ የዉሃ ሙሌት መጀመሩን የኢፌደሪ የዉሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገለጹ፡፡
የዉሃ ሙሌቱ የግድቡን ተፈጥሯዊ የግንባታ ሂደት በጠበቀ መልኩ እየተከናወነ መሆኑንም ሚኒስትሩ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ማብራራታቸውን ኢቢሲ እና ፋናን ጨምሮ የተለያዩ የሀገሩስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡
አሁን ላይ ግድቡን በተመለከተ በሳተላይት የሚታዩ ምስሎች ትክክለኛ መሆናቸውንም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡
የአውሮፓ ስፔስ ኤጀንሲው ሴንቲኔል-1 ከቀናት በፊት የግድቡ የዉሃ ሙሌት መጀመሩን የተመለከተ የሳተላይት ምስል አውጥቷል፡፡ ይሄን ምስል መነሻ ያደረጉ ትንታኔዎች በተለያዩ ሚዲያዎች ሲሰጡም ነበር፡፡
የሴንቲኔል-1 የሳተላይት ምስል-ፎቶ ከአሶሼትድ ፕሬስ
የኢትዮጵያ መንግስት የህዳሴ ግድቡን የዉሃ ሙሌት እጀምራለሁ ባለው ጊዜ ሙሌቱን ማከናወን ጀምሯል፡፡ በዚህም መሰረት ግድቡ በዚህ ዓመት 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ዉሃ እንደሚይዝ መንግስት ከዚህ ቀደም መግለጹ ይታወቃል፡፡ ግድቡ ዉሃ ለመያዝ በሚያስችለው የግንባታ ከፍታ ላይ መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ገልጸዋል፡፡
ግንባታው ሲጠናቀቅ 1,800 ሜትር ርዝመት እና ከ145 እስከ 170 ሜትር የመጨረሻ ከፍታ የሚኖረው ሲሆን አጠቃላይ የሚይዘው የዉሃ መጠንም 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ነው፡፡
የግድቡን የመጀመሪያ የዉሃ ሙሌት እና ዓመታዊ አለቃቀቅ በተመለከተ በኢትዮጵያ ሱዳን እና ግብፅ መካከል ስምምነት ያልተደረሰባቸው በርካታ ነጥቦች አሉ፡፡
ግብፅ እና ሱዳን የግድቡ የመጀመሪያ ደረጃ የዉሃ ሙሌት የሶስትዮሽ ስምምነት ሳይደረስ እንዳይጀመር በሚል አቋማቸው የጸኑ ቢሆንም ፣ ኢትዮጵያ በበኩሏ ፣ ስምምነት ተደረሰም አልተደረሰ፣ በሁለቱ ሀገራት ላይ ጉልህ ተጽዕኖ በማያደርስ መልኩ በክረምት ወቅት ሙሌቱን እንደምትጀምር ስትገልጽ ቆይታለች፡፡
በሶስቱ ሀገራት መካከል በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ለ11 ቀናት ሲካሄድ የነበረው ድርድርም ከትናንት በስቲያ ያለስምምነት ተጠናቋል፡፡ በድርድሩ ሂደት ደቡብ አፍሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ እንዲሁም በአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 11 ባለሙያዎች በታዛቢነት ተሳትፈዋል፡፡
ይሄንኑ ድርድር በተመለከተ ትናንት ሐምሌ 7 ቀን 2012 ዓ.ም. መግለጫ ያወጣው የዉሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የግብፅ እና የሱዳን “ግትር አቋም” እና “ተጨማሪ ከፍተኛ ፍላጎት” ማንጸባረቃቸውን ስምምነት ላለመደረሱ በምክንያትነት አስቀምጧል፡፡
በኢትዮጵያ ወገን ግን ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ላይ ለመድረስ መለሳለሶች መታየታቸውንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
ግብፅና ሱዳን በበኩላቸው ለስምምነቱ አለመደረስ “ግትር አቋም ይዛለች” ያሏትን ኢትዮጵያን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡
በድርድሩ ላይ በተወሰኑ ነጥቦች መግባባት ላይ መደረሱን ዛሬ በሰጡት መግለጫ የገለፁት ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ “ኢትዮጵያ አሁንም አለመግባባቶች የሶስቱንም ሀገራት የጋራ ጥቅም ሊያስጠብቅ በሚችል ድርድር ብቻ እንደሚፈታ ታምናለች” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
የኢፌደሪ የዉሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ፣ ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የምታደርገው ድርድር የአሁኑን ትውልድ ብቻ ሳይሆን የመጪውን ትውልድ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልከ የሚደረግ እንደሆነም አብራርተዋል።
ግብፅ ግድቡ ከአባይ ወንዝ የማገኘውን የዉሃ መጠን ይቀንስብኛል፤ ይሔም ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ቀውስ ያስከትልብኛል የሚል እምነት ሲኖራት ኢትዮጵያ ደግሞ ግብፅና ሱዳን ላይ ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መልኩ የተፈጥሮ ሀብቴን እጠቀማለሁ የሚል ጽኑ አቋም ይዛለች፡፡