ኢትዮጵያ የምትቀበላቸው ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ ቢሆንም አለማቀፍ ድጋፉ ግን በየአመቱ እየቀነሰ ነው ተባለ
በ2022 ለስደተኞች የተያዘው በጀት በ2017 ከነበረበት በ1/3ኛ መቀነሱንም የስደተኞችና ከስደት ተመላሽ አገልግሎት ገልጿል
ኢትዮጵያ ከ27 ሀገራት የመጡ 1 ሚሊዮን ገደማ ስደተኞችን ታስተናግዳለች
የ1951ዱን የስደተኞች ኮንቬንሽንና የ1967ቱን ፕሮቶኮል የፈረመችው ኢትዮጵያ ፣ ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን /ዩኤንኤችሲአር/ እና ሌሎች ባለድርሻ አካለት ጋር በመሆን ስደተኞችን በመቀበል ዓለም አቀፋዊ ኃላፊነቷን እየተወጣች ትገኛለች፡፡
ኢትዮጵያ ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም አቀፍ ሰላም ከምታበረክተው አስተዋጽኦ ባለፈ ስደተኞችን በማስተናገድ የምትወጣው ኃላፊነት በብዙዎች ዘንድ ያስመሰገናትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አመኔታና ክብር እንድታገኝም ያስቻላት መሆኑ ይታወቃል፡፡
አሁን ላይ ከ27 ሀገራት በተለይም ከደቡብ ሱዳን ፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ የመጡ 883 ሺህ ስደተኞች ተቀብላም እያስተናገደች ነው ኢትዮጵያ፡፡ ይህ ባሳለፍነው ወርሃ የካቲት በሶማሊላንድ የተነሳውን ግጭት በመሸሽ ድንበር ተሻግረው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው እየተነገረ ያለውን 100 ሺህ ሶማሊያውያን ሳይጨምር መሆኑ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረውን ስደተኞችን የመቀበል ልምዷን ተጠቅማ 1 ሚሊየን ለሚጠጉ ስደተኞች መጠለያ ሆና ማገልገሏን ብትቀጥልም፤ አሁን ላይ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በቂ ድጋፍ እያገኘች አይደለም።
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን መረጃ እንደሚያመለክተው በፈረንጆቹ 2022 በኢትዮጵያ ከስደተኞች ጋር በተያያዘ ስራዎችን ለመስራት 365 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልግ የነበረ ቢሆንም ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊገኝ የቻለው ድጋፍ ግማሹ ብቻ ነበር፡፡
ከአል-ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት የስደተኞችና ከስደት ተመላሽ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ፤ ኢትዮጵያ ለዓለም ከምታበረክተው አስተዋጽኦ አንጻር የምታገኘው ድጋፍ በቂ አይደለም የሚለውን ሃሳብ እንደሚጋሩ ተናግረዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ የኢትዮጵያ መንግስት የሚያገኘው ድጋፍ በተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ ስደተኞች ኮሚሽን በኩል መሆኑን ገልጸው፤ የሚደረገው ድጋፍ በተለይም ከቅርብ አመታት ወዲህ እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
ከ2017 ጀምሮ ላለፉት ስድስት አመታት በጀት እየቀነሰ በተቃራኒው የስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መጥቷልም ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ተስፋሁን፡፡
“በ2017 የስደተኞች ቁጥር 742 ሺህ ነበር፤ በወቅቱ የነበረው የኦፕሬሽን በጀት አሁን የስደተኞች ቁጥር 883 ሺህ በደረሰበት ካለው በጀት አንጻር ስናይ በሶስት እጥፍ ቀንሷል፤ ስደተኛው በ100 ሺህ ቢጨምርም በጀቱ በ2017 ከነበረበት በብዙ እጥፍ የቀነሰ ነው” ሲሉም አብራርተዋል፡፡
ዓለም ባለፉት አመታት ዓይኑን ወደ አፍጋኒስታን እና ዩክሬን ማዞሩ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአፍሪካ ስደተኞች የሚሰጠው ትኩረት አናሳ እንዲሆን እንዳደረገውም በምክንያትነት አንስተዋል፡፡
“በዓለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኞችን የሚያስተዳድሩት በልማት ኋላ የቀሩት ወይም ታዳጊ ሀገራት ሆነው ሳለ እነሱን የሚያግዝ ፓኬጅ አለመኖሩ የሚሳዝን ነው”ም ብለዋል፡፡
በቂ ድጋፍ ባለመኖሩ ስደተኞች አስፈላጊውን ሰብአዊ ድጋፍ እንደማያገኙና ተቀባይ ማህበረሰቦችም ከችግሮቻቸው እየተላቀቁ እንዳልሆነ ነው ያብራሩት።
“ለአብነትም በጋምቤላ አንድ ሆስፒታል ነው ያለው፤ ያለው የህዝብ ብዛት 470 ሺህ ነው፤ ያለው ስደተኛም 400 ሺህ ገደማ ነው፤ ስለዚህም ስደተኛው ብቻውን አንድ ሪፈራል ሆስፒታል ያስፈልገዋል ማለት ነው፤ እነዚህ ነገሮች ጫና ይፈጥራሉ፡፡ ይህ ሄዶ ሄዶ በተቀባይ ማህበረሰብ እና በስደተኛው መካከል ያለውን ግንኙነት ፡ሊያሻክር ስለሚችል በቂ ድጋፍ መኖር አለበት”ሲሉም አሳስበዋል።
የስደተኞችና ከስደት ተመላሽ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ፥ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ለተሰደዱ ዜጎቻቸው ያቀረቡትን ጥሪ ጥሪ በተመለከተም አስተያየታቸው ሰንዝረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙ ደቡብ ሱዳናውያን ስደተኞች የምታስተናግድ እንደመሆኗ የፕሬዝዳንቱን ጥሪ በበጎ ትመልከተዋለች ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፥ ቀደም ሲል የኢትዮጵያ መንግስት ከኢጋድ ጋር በመተባበር የደቡብ ሱዳን ኢኒሼቲቭ የሚል ፕሮጄክት ተቀርጾ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አውስተዋል።
“የፕሬዝዳንቱን ጥሪ ተቀብለው መሄድ የሚፈልጉ ስደተኞች ካሉ በእኛ በኩል ነገሮችን አመቻችተን እስከ ድንበር ድረስ ለመሸኘት ዝግጁ ነን”ም ነው ያሉት።
አቶ ተስፋሁን ከስደተኞች ጋር በተያያዘ የሚነሱ የጸጥታ ችግሮች በተመለከተ ሲናገሩም አልፎ አልፎ የሚያግጥሙ ችግሮች መኖራቸው አምነዋል፡፡
ስደተኞች በሚኖርባቸው አከባቢዎች ከተቀባይ ማህበረሰብ ጋር ጥሩ የሚባል መስተጋብር እንዲኖራቸው የኢትዮጵያ መንግስት ፍላጎት መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ፤ በቅርቡ ከደቡብ ሱዳን ስደተኞች ጋር ተያይዞ በጋምቤላ ክልል ዲማ ወረዳ አከባቢ ላይ ችግሮች ተፈጥረው እንደነበር ለአብነት አንስተዋል፡፡
“ሁሉም ጥፋት የስደተኞች ችግር አይደለም፤ በሙርሌ እና አኝዋክ ጎሳ መካከል የሚነሳ ግጭት አለ፤ ግጭቱ ደቡብ ሱዳን ላይ ሊከሰት ይችላል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ካምፖችም ሊከሰት ይችላል፤ ከዛ የመበቃቀል እርምጃ ካምፕ ውስጥ አንዳንዴ ያጋጥማል፤ ካምፕ ውስጥ አኝዋኩ ተገደልኩ ብሎ ሲያምን ሙርሌውን መግደል ሙርሌው ደግሞ ተገደልኩ ብሎ አኝዋኩን (የመግደል) ሙከራዎች ታይተዋል” ሲሉም ነው የገለጹት፡፡
ያም ሆኖ አልፎ አልፎ የሚያገጥመውን ችግር ለመቅረፍ ከክልሉ የጸጥታ መዋቅር ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
እስካሁን በተሰሩ ስራዎች ብዙ ግጭቶችን ማስቀረት እንደተቻለና ከተከሰቱ በኋላም ቢሆን በአጥፊዋች ላይ የእርምት እርምጃ እንደተወሰደ ተናግረዋል ዋና ዳይሬክተሩ፡፡